በዚያኑ ጊዜ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ ሊሞት ተቃርቦ ነበር፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እግዚአብሔርም እንደሚያድነው የሚያረጋግጥ ምልክት አሳየው። ሕዝቅያስ ግን ልቡ በትዕቢት ተሞልቶ ስለ ነበር፥ እግዚአብሔር ስላደረገለት ቸርነት ሁሉ ተገቢ ምስጋና አላቀረበም፤ ከዚህም የተነሣ በእርሱ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ሕዝብ ብርቱ ሥቃይ ደረሰባቸው። ይሁን እንጂ በመጨረሻ ሕዝቅያስና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በትሕትና ራሳቸውን ስላዋረዱ ሕዝቅያስ ከዚህ ዓለም በሞት እስከ ተለየበት ጊዜ ድረስ እግዚአብሔር ሕዝቡን አልቀጣም። ንጉሥ ሕዝቅያስ እጅግ በለጸገ፤ ሕዝቡም ሁሉ አከበሩት፤ ወርቁን፥ ብሩን፥ የከበረ ዕንቊውን፥ ቅመማ ቅመሙን፥ ጋሻዎቹንና ሌሎቹንም ውድ የሆኑ ዕቃዎቹን የሚያኖርባቸው ዕቃ ግምጃ ቤቶችን ሠራ፤ በተጨማሪም ለእህሉ፥ ለወይን ጠጁና ለወይራ ዘይቱ ማኖሪያ የሚሆኑ የዕቃ ግምጃ ቤቶችን፥ ለቀንድ ከብቶቹ በረት፥ ለበጎቹም ጒረኖ ሠርቶ ነበር፤ ከዚህም ሁሉ ሌላ እግዚአብሔር ብዙ የቀንድ ከብትና የበግ መንጋ እንዲሁም ሌላ እጅግ የበዛ ሀብት ስለ ሰጠው፥ ብዙ ከተሞችን ሠራ፤ በላይ በኩል ያለውን የግዮንን ምንጭ መውጫ ገድቦ ውሃውን ወደ ምዕራብ፥ ወደ ዳዊት ከተማ፥ በቦይ እንዲወርድ ያደረገ ራሱ ሕዝቅያስ ነው፤ ይህ ሕዝቅያስ ሊሠራ ባቀደው ነገር ሁሉ የተሳካለት ሰው ነበር፤ ነገር ግን የባቢሎን መልእክተኞች በአገሪቱ ስለ ተደረገው አስደናቂ ነገር ሊጠይቁት ወደ እርሱ መጥተው በነበረ ጊዜ እግዚአብሔር በሕዝቅያስ ልብ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ለማወቅ ይፈትነው ዘንድ ተወው። ንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ ለእግዚአብሔርም የነበረው መንፈሳዊ ቅናት በአሞጽ ልጅ በነቢዩ ኢሳይያስ ራእይ እንዲሁም በይሁዳና በእስራኤል የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግበው ይገኛሉ። ሕዝቅያስ ሞተ፤ በላይኛው ክፍል በሚገኘውም በዳዊት ልጆች መካነ መቃብር ተቀበረ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብም ሁሉ ታላቅ የቀብር ሥነ ሥርዓት አደረጉለት፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ምናሴ ነገሠ።
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 32 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 32:24-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች