ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 28
28
የይሁዳ ንጉሥ አካዝ
(2ነገ. 16፥1-4)
1አካዝ ዕድሜው ኻያ ዓመት ሲሆን ነገሠ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ፤ የቀድሞ አባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም ምሳሌነትን ባለመከተሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አላደረገም፤ 2የእስራኤልን ነገሥታት መጥፎ አርአያነት ተከተለ፤ ባዓል ተብሎ የሚጠራ የጣዖት ምስሎችን አቅልጦ ሠራ፤ 3በሂኖም ሸለቆም ዕጣን አጠነ፤ እስራኤላውያን ወደ ምድሪቱ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ከዚያ ያባረራቸውን ሕዝቦች አጸያፊ ልማድ በመከተል፥ የራሱን ወንዶች ልጆች እንኳ ሳይቀር የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ለጣዖቶች አቀረበ። 4በኰረብቶች ላይ በሚገኙ በአሕዛብ የማምለኪያ ስፍራዎችና በየዛፉ ጥላ ሥር መሥዋዕትን አቀረበ፤ ዕጣንንም አጠነ።
በሶርያና በእስራኤል ላይ የተደረገ ጦርነት
(2ነገ. 16፥5)
5-6ንጉሥ አካዝ ኃጢአት ስለ ሠራ የሶርያ ንጉሥ ድል እንዲያደርገውና ብዙ ወገኖቹን እስረኞች አድርጎ ወደ ደማስቆ እንዲወስድ እግዚአብሔር ፈቀደ፤ እንዲሁም የረማልያ ልጅ የሆነው የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ አካዝን ድል እንዲያደርግና እጅግ በጣም ጀግኖች ከሆኑ ከይሁዳ ወታደሮች መካከል በአንድ ቀን መቶ ኻያ ሺህ እንዲገድል እግዚአብሔር ፈቀደ፤ የቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ይህን የፈቀደበት ምክንያት የይሁዳ ሰዎች እርሱን ስለ ተዉ ነው። #ኢሳ. 7፥1። 7ዚክሪ ተብሎ የሚጠራ አንድ እስራኤላዊ ወታደር የንጉሥ አካዝን ልጅ ማዕሤያን፥ የቤተ መንግሥቱን አስተዳዳሪ ዓዝሪቃምንና በሥልጣን ከንጉሡ ሁለተኛ የሆነውን ሕልቃናን ገደለ፤ 8አይሁድ ወገኖቻቸው ቢሆኑም እንኳ የእስራኤል ወታደሮች ሁለት መቶ ሺህ ሴቶችንና ሕፃናትን እስረኞች አድርገው ከብዙ ምርኮ ጋር ወደ ሰማርያ ወሰዱአቸው።
ነቢዩ ዖዴድ
9የእግዚአብሔር ነቢይ የሆነ፥ ዖዴድ ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው በሰማርያ ከተማ ይኖር ነበር፤ የእስራኤል ሠራዊት አይሁድን እስረኞች አድርገው በመውሰድ ወደ ሰማርያ ከተማ በመግባት ላይ ሳሉ ወደ እነርሱ መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “የቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በይሁዳ ሕዝብ ላይ ስለ ተቈጣ እነርሱን ድል እንድታደርጉአቸው አደረገ፤ እናንተ ግን ወደ ሰማይ በደረሰ ቊጣ ፈጃችኋቸው፤ 10ይህም አልበቃ ብሎአችሁ የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ወንዶችና ሴቶች በሙሉ የእናንተ ባሪያዎች ልታደርጉአቸው ታስባላችሁ፤ እናንተስ ይህን ስታደርጉ ኃጢአት በመሥራት አምላካችሁን እግዚአብሔርን ማሳዘናችሁ አይደለምን? 11አሁንም እነሆ አድምጡኝ! የእግዚአብሔር ቊጣ በእናንተ ላይ ስለ ነደደ እነዚህ እስረኞች ወንድሞቻችሁንና እኅቶቻችሁን ወደየመኖሪያ ስፍራቸው ተመልሰው ይሄዱ ዘንድ ልቀቁአቸው።”
12እንዲሁም የይሆሐናን ልጅ ዐዛርያስ፥ የመሺሌሞት ልጅ ቤሬክያ፥ የሻሉም ልጅ የይሒዝቂያና የሐድላይ ልጅ ዐማሣ የተባሉት አራት የታወቁ የኤፍሬም ግዛት መሪዎች የሠራዊቱን ድርጊት ተቃወሙ፤ 13እንዲህም አሉአቸው፦ “እነዚህን እስረኞች ወደዚህ አታምጡብን! ከዚህ ቀደም ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን ስላሳዘንን ቊጣው በእኛ ላይ ወርዶአል፤ አሁንም በበደል ላይ በደል እንድንፈጽም ትፈልጋላችሁን?” 14ስለዚህ ሠራዊቱ እስረኞቹንና ምርኮውን ለሕዝቡና ለመሪዎቻቸው አስረከቡ። 15ከዚያም በኋላ እነዚያ አራት ሰዎች ለእስረኞቹ ከምርኮው አስፈላጊውን ነገር ሁሉ እንዲሰጡ ተመደቡ፤ እነርሱም ራቊታቸውን ለቀሩት እስረኞች ልብስና ጫማ፥ እንዲሁም በቂ ምግብና ውሃ ሰጡአቸው፤ በቊስላቸውም ላይ የወይራ ዘይት በማፍሰስ ርዳታ አደረጉላቸው፤ በእግር ለመሄድ የማይችሉትን ደካሞችንም በአህያ ላይ አስቀመጡአቸው፤ እስረኞቹም ሁሉ በይሁዳ ግዛት ወደምትገኘው፥ የዘንባባ ዛፍ በብዛት ወደሚገኝባት ወደ ኢያሪኮ ከተማ መልሰው ወሰዱአቸው፤ ከዚህም በኋላ እስራኤላውያን ወደ መኖሪያ ከተማቸው ወደ ሰማርያ ተመለሱ።
አካዝ የአሦርን ርዳታ መለመኑ
(2ነገ. 16፥7-9)
16-17ኤዶማውያን የይሁዳን ግዛት እንደገና በመውረር ብዙ ሰዎችን ማርከው ወሰዱ፤ ስለዚህ ንጉሥ አካዝ ርዳታ እንዲልክለት የአሦርን ንጉሠ ነገሥት ለመነ። 18በዚሁ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን በምዕራባዊ ኰረብቶች ግርጌና በደቡባዊ ይሁዳ የሚገኙትን ታናናሽ ከተሞች ወረሩ፤ ቤትሼሜሽ፥ አያሎን፥ ገዴሮት፥ ሶኮ፥ ቲምናና ጊምዞ ተብለው የሚጠሩትን ከተሞችና በዙሪያቸው የሚገኙትን መንደሮች በድል አድራጊነት ያዙ፤ በዚያም ኖሩ። 19የይሁዳ ንጉሥ አካዝ በሀገሩ ላይ ክፉ ነገርን ስላስፋፋና ለእግዚአብሔር የነበረውን ታማኝነት ስላጐደለ፥ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ችግርና መከራ እንዲወርድ ፈቀደ። 20የአሦር ንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴርም አካዝን በመርዳት ፈንታ ተቃወመው፤ ችግርም አመጣበት፤ 21ስለዚህ አካዝ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፥ ከቤተ መንግሥቱና ከሕዝቡ መሪዎች ዘንድ ብዙ ወርቅ ወስዶ ለንጉሠ ነገሥቱ መማለጃ አድርጎ ሰጠ፤ ይሁን እንጂ ይህን ማድረጉም አልጠቀመውም።
አካዝ የሠራው ኃጢአት
22አካዝ፥ ችግሩ እየባሰበት በሄደ ጊዜ ከምንጊዜውም ይበልጥ ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ። 23አካዝ ድልን ላጐናጸፉአቸው ለሶርያውያን አማልክት መሥዋዕት አቀረበ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት “የሶርያ አማልክት የሶርያን ነገሥታት ረድተዋል፤ መሥዋዕት ባቀርብላቸው እኔንም ይረዱኛል” ብሎ በማሰብ ነው፤ ይህም ድርጊት በራሱና በሀገሩ ላይ ጥፋትን አመጣ፤ 24በተጨማሪም አካዝ የቤተ መቅደሱን ዕቃ ሁሉ አውጥቶ ሰባበረው፤ ቤተ መቅደሱንም ዘጋ፤ በኢየሩሳሌምም በየስፍራው የጣዖት መሠዊያዎችን አቆመ፤ 25በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ለባዕዳን አማልክት ዕጣን የሚታጠንባቸውን የኰረብታ የማምለኪያ ስፍራዎችን ሠራ፤ በዚህም ሁኔታ አካዝ የቀድሞ አባቶቹን አምላክ የእግዚአብሔርን ቊጣ በራሱ ላይ አመጣ።
26በአካዝ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተፈጸመው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግቦ ይገኛል። 27ንጉሥ አካዝ ሞተ፤ በኢየሩሳሌምም ተቀበረ፤ ይሁን እንጂ በነገሥታት መካነ መቃብር አልተቀበረም፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ሕዝቅያስ ነገሠ። #ኢሳ. 14፥28።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 28: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997