ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 23:16-21

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 23:16-21 አማ05

ካህኑ ዮዳሄ ራሱ እንዲሁም ንጉሥ ኢዮአስና ሕዝቡ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆናቸውን ለማደስ ቃል ኪዳን እንዲገቡ አደረገ። ከዚህም በኋላ ሁሉም በአንድነት ባዓል ተብሎ ወደሚጠራው ቤተ ጣዖት ሄደው አፈረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሁሉ ሰባበሩ፤ ማታን ተብሎ የሚጠራውንም የባዓል ካህን በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት። ዮዳሄ ካህናቱንና ሌዋውያኑን የቤተ መቅደሱ ሥራ ኀላፊዎች እንዲሆኑ አደረገ፤ የእነርሱም ተግባር በንጉሥ ዳዊት የተመደበላቸውን ሥራ ማከናወንና በኦሪት ሕግ መሠረት ለእግዚአብሔር የሚቀርቡትን መሥዋዕት ማቃጠል ነበር፤ እንዲሁም በዳዊት መመሪያ መሠረት የዜማና የበዓል አከባበር ሥነ ሥርዓት ኀላፊነት ተሰጥቶአቸው ነበር፤ ዮዳሄ ያልነጻ ማንኛውም ሰው ወደ ቤተ መቅደስ እንዳይገባ በቤተ መቅደሱ ቅጽር በሮች ሆነው የሚጠብቁ ዘበኞችን መድቦ ነበር። የጦር መኰንኖቹ፥ የታወቁ የአገር ሽማግሌዎች የመንግሥት ባለሥልጣኖችና የቀሩትም ሕዝብ ሁሉ ከዮዳሄ ጋር በመሆን ከቤተ መቅደስ እስከ ቤተ መንግሥት ድረስ ንጉሡን አጅበው ሄዱ፤ በቤተ መንግሥቱም ዋና በር ገቡ፤ ንጉሡም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በታላቅ ደስታ ተሞሉ፤ ዐታልያም ተገድላ ስለ ነበር ከተማይቱ ሰላም ሰፍኖባት ጸጥ ብላ ነበር።