ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 23
23
በዐታልያ ላይ የተደረገ ዐመፅ
(2ነገ. 11፥4-16)
1ካህኑ ዮዳሄ በሰባተኛው ዓመት የመቶ አለቆች ከነበሩት ከይሮሖም ልጅ ዐዛርያስ፥ ከይሆሐናን ልጅ እስማኤል፥ ከዖቤድ ልጅ ዐዛርያስ፥ ከዐዳያ ልጅ ማዕሴያና ከዚክሪ ልጅ ኤሊሻፋጥ ጋር ስምምነት ለማድረግ ብቃት ያለው መሆኑ ተሰማው፤ 2እነርሱም ወደ መላው የይሁዳ ከተማዎች ተጒዘው ሌዋውያንና የጐሣ መሪዎችን ሁሉ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
3ሁሉም በአንድነት በቤተ መቅደሱ ተሰብስበው ከንጉሡ ልጅ ከኢዮአስ ጋር የስምምነት ውል አደረጉ፤ ካህኑ ዮዳሄ እንዲህ አላቸው፦ “እግዚአብሔር ለዳዊት ‘ልጆችህ ለዘለቄታ ይነግሣሉ’ ሲል በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት አሁን መንገሥ ያለበት ኢዮአስ ነው፤ #2ሳሙ. 7፥12። 4አሁን ማድረግ ያለብንም ይኸው ነው፤ ካህናትና ሌዋውያን በሰንበት ቀን አገልግሎታቸውን ለማከናወን በሚመጡበት ጊዜ ከእነርሱ አንድ ሦስተኛው እጅ የቤተ መቅደሱን ቅጽር በሮች ይጠብቅ፤ 5ሌላው አንድ ሦስተኛ እጅ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቅ፤ የመጨረሻው አንድ ሦስተኛ እጅ የመሠረት ቅጽር በር ተብሎ የሚጠራውን ስፍራ ይጠብቅ፤ ሕዝቡም ሁሉ በቤተ መቅደሱ አደባባይ ውስጥ ይሰብሰቡ፤ 6በአገልግሎት ላይ ከሚገኙት ካህናትና ሌዋውያን በቀር ማንም ሰው ወደ ቤተ መቅደሱ መግባት የለበትም፤ ካህናትና ሌዋውያን ግን ለእግዚአብሔር የተለዩ ስለ ሆኑ መግባት ይፈቀድላቸዋል፤ የቀሩት ሰዎች የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመፈጸም ከቤተ መቅደሱ ውጪ ይሁኑ። 7ሌዋውያን ሰይፎቻቸውን በእጆቻቸው በመያዝ ዙሪያውን ሆነው ንጉሡን ይጠብቁት፤ ንጉሡ ወደሚሄድበትም ቦታ ሁሉ አብረው ይሂዱ፤ ወደ ቤተ መቅደስ ለመግባት የሚሞክር ማንኛውም ሰው ይገደል።”
8ሌዋውያንና የይሁዳ ሕዝብ ካህኑ ዮዳሄ የሰጣቸውን መመሪያ ሁሉ ፈጸሙ፤ ዮዳሄም አገልግሎታቸውን ፈጽመው በሰንበት ቀን ከሥራ ነጻ መሆን የሚገባቸው ሌዋውያን አላሰናበታቸውም ነበር፤ ስለዚህ ለዘብ ጥበቃ የሚሰማሩትና ከዘብ ጥበቃ ነጻ የሆኑት እዚያው ስለ ነበሩ የጦር መኰንኖቹ በቂ ሰዎች ነበሩአቸው፤ 9ዮዳሄም በቤተ መቅደስ ተጠብቀው ይኖሩ የነበሩትን የንጉሥ ዳዊትን ጦሮችና ጋሻዎች ለጦር መኰንኖች ሰጣቸው፤ 10ሰይፋቸውን በእጃቸው ያያዙትን ጭፍሮች ሁሉ ንጉሡን ከአደጋ ለመከላከል በመሠዊያው በኩል በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ዙሪያውን ተሰልፈው እንዲቆሙ አደረጋቸው። 11ከዚህ በኋላ ዮዳሄ ኢዮአስን አውጥቶ በራሱ ላይ ዘውድ ጫነበት፤ ለመንግሥቱ መመሪያ የሆነውንም ሕግ አንድ ቅጅ አስረከበው፤ በዚህ ዐይነት ካህኑ ዮዳሄና ልጆቹ ኢዮአስን ቀብተው አነገሡት፤ ሕዝቡም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ረጅም ዕድሜ ለንጉሡ!” በማለት ደስታቸውን ገለጡ።
12ዐታልያ ሕዝቡ ለንጉሡ ያደረገውን እልልታና ሆታ ሰምታ ሕዝብ ወደ ተሰበሰበበት ወደ ቤተ መቅደስ በፍጥነት መጣች። 13እዚያም እንደ ደረሰች አዲሱ ንጉሥ በተለመደው ባህል መሠረት ለነገሥታት በተመደበው በቤተ መቅደሱ መግቢያ በሚገኘው ዐምድ አጠገብ በጦር መኰንኖችና በእምቢልታ ነፊዎች ተከቦ ታጅቦ እንደ ቆመ አየች፤ ሕዝቡም ሁሉ በደስታ ተሞልተው እልል ይሉ ነበር፤ እምቢልታ ነፊዎችም መለከት ይነፉ ነበር፤ የቤተ መቅደስ መዘምራንም በሙዚቃ መሣሪያዎች ታጅበው የበዓሉን ሥነ ሥርዓት ይመሩ ነበር፤ ዐታልያም በድንጋጤ ልብስዋን በመቅደድ “ይህ ሤራ ነው! ይህ ሤራ ነው!” ስትል ጮኸች።
14ዮዳሄ በበኩሉ ዐታልያ በቤተ መቅደሱ ክልል ውስጥ እንድትገደል አልፈለገም፤ ስለዚህም የጦር መኰንኖቹን ጠርቶ “ግራና ቀኝ በተሰለፉት ዘቦች መካከል አውጥታችሁ ውሰዱአት፤ እርስዋን ከሞት ለማትረፍ የሚሞክር ሰው ቢኖር ግደሉት” ሲል አዘዛቸው።
15እነርሱም እርስዋን አፈፍ አድርገው በመያዝ ወደ ቤተ መንግሥት ወሰዱአት፤ እዚያም “የፈረስ መግቢያ ቅጽር በር” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ገደሉአት።
ዮዳሄ ያደረገው መሻሻል
(2ነገ. 11፥17-20)
16ካህኑ ዮዳሄ ራሱ እንዲሁም ንጉሥ ኢዮአስና ሕዝቡ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆናቸውን ለማደስ ቃል ኪዳን እንዲገቡ አደረገ። 17ከዚህም በኋላ ሁሉም በአንድነት ባዓል ተብሎ ወደሚጠራው ቤተ ጣዖት ሄደው አፈረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሁሉ ሰባበሩ፤ ማታን ተብሎ የሚጠራውንም የባዓል ካህን በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት።
18ዮዳሄ ካህናቱንና ሌዋውያኑን የቤተ መቅደሱ ሥራ ኀላፊዎች እንዲሆኑ አደረገ፤ የእነርሱም ተግባር በንጉሥ ዳዊት የተመደበላቸውን ሥራ ማከናወንና በኦሪት ሕግ መሠረት ለእግዚአብሔር የሚቀርቡትን መሥዋዕት ማቃጠል ነበር፤ እንዲሁም በዳዊት መመሪያ መሠረት የዜማና የበዓል አከባበር ሥነ ሥርዓት ኀላፊነት ተሰጥቶአቸው ነበር፤ 19ዮዳሄ ያልነጻ ማንኛውም ሰው ወደ ቤተ መቅደስ እንዳይገባ በቤተ መቅደሱ ቅጽር በሮች ሆነው የሚጠብቁ ዘበኞችን መድቦ ነበር።
20የጦር መኰንኖቹ፥ የታወቁ የአገር ሽማግሌዎች የመንግሥት ባለሥልጣኖችና የቀሩትም ሕዝብ ሁሉ ከዮዳሄ ጋር በመሆን ከቤተ መቅደስ እስከ ቤተ መንግሥት ድረስ ንጉሡን አጅበው ሄዱ፤ በቤተ መንግሥቱም ዋና በር ገቡ፤ ንጉሡም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ 21ሕዝቡም ሁሉ በታላቅ ደስታ ተሞሉ፤ ዐታልያም ተገድላ ስለ ነበር ከተማይቱ ሰላም ሰፍኖባት ጸጥ ብላ ነበር።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 23: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997