ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 2:1-6

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 2:1-6 አማ05

ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስና ለራሱ ቤተ መንግሥት ለመሥራት ወሰነ፤ ስለዚህም ዕቃን የሚያጓጒዙ ሰባ ሺህ፥ ድንጋይ የሚፈልጡ ሰማኒያ ሺህ ሰዎችን በሥራ ላይ አሰማራ፤ ሥራውን የሚቈጣጠሩ ደግሞ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎችን መደበ። ከዚህም በኋላ ለጢሮስ ንጉሥ ኪራም የሚከተለውን መልእክት ላከ፤ “አባቴ ንጉሥ ዳዊት ቤተ መንግሥቱን በሠራበት ጊዜ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ትልክለት እንደ ነበር ለእኔም ላክልኝ፤ አሁን እኔ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስን ለመሥራት በመዘጋጀት ላይ ነኝ፤ ይህም ቤተ መቅደስ እኔና ሕዝቤ በእግዚአብሔር ፊት ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን የምናጥንበት የተቀደሰውን ኅብስት ሳናቋርጥ ለእግዚአብሔር የምናቀርብበት፥ በየቀኑ ጠዋትና ማታ፥ እንዲሁም በሰንበቶች፥ በወር መባቻዎችና በሌሎችም በተቀደሱ በዓላት እግዚአብሔር አምላካችንን ለማክበር የሚቃጠለውን መሥዋዕት የምናቀርብበት የተቀደሰ ስፍራ ይሆናል፤ የእስራኤል ሕዝብ ይህን ለዘለዓለም እንዲያደርጉ እግዚአብሔር አዞአል። የእኛ አምላክ ከሌሎች አማልክት ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ስለ ሆነ ታላቅ ቤተ መቅደስ ልሠራለት ዐቅጃለሁ። እንደ እውነቱ ከሆነ ለእግዚአብሔር በቂ የሚሆን ቤተ መቅደስን ለመሥራት የሚችል ማንም የለም፤ የሰማይና የምድር ስፋት እንኳ እግዚአብሔርን ሊይዘው አይችልም፤ ታዲያ ለእግዚአብሔር ዕጣን ለማጠን የሚበቃ ቤት ከመሥራት በቀር ለእርሱ ማደሪያ ሊሆን የሚችል ቤተ መቅደስ ለመሥራት የምሞክር እኔ ማን ነኝ?