የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 14

14
የይሁዳ ንጉሥ አሳ ኢትዮጵያውያንን ድል ማድረጉ
1ንጉሥ አቢያ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘውም በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አሳ ነገሠ፤ በአሳም ዘመነ መንግሥት በምድሪቱ ላይ ለዐሥር ዓመት ሰላም ሆነ፤ 2አሳ በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን የሆነውን ነገር አደረገ፤ 3ባዕዳን መሠዊያዎችንና በኰረብቶች ላይ የነበሩትን የአሕዛብ የማምለኪያ ስፍራዎችን አስወገደ፤ ለማምለኪያ የተሠሩ የድንጋይ ዐምዶችን ሰባበረ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስሎችን አንከታክቶ ጣለ፤ 4አሳ የይሁዳ ሰዎች የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲፈጽሙ፥ ሕጉንና ትእዛዞቹን እንዲጠብቁ አዘዘ፤ 5የኰረብታ መስገጃዎች ስፍራዎችንና ዕጣን የሚታጠንባቸውን መሠዊያዎች ከይሁዳ ከተሞች ሁሉ ስላስወገደ፥ በእርሱ ዘመነ መንግሥት ሰላም ሰፈነ፤ 6ለይሁዳ ከተሞች ምሽጎችን ሠራ፤ እግዚአብሔር ሰላም ስለ ሰጠውም ለብዙ ዘመን በአገሪቱ ጦርነት አልነበረም፤ 7አሳ የይሁዳን ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “ግንቦችን፥ ቅጽሮችንና በብረት መወርወሪያ የሚዘጉ የቅጽር በሮችን በመሥራት፥ ከተሞቻችንን እንመሽግ፤ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስለ ፈጸምን፥ እነሆ፥ ምድሪቱ በቊጥጥራችን ሥር ናት፤ እግዚአብሔር ጠብቆናል፤ በሁሉም አቅጣጫ የሰላም ዋስትና ሰጥቶናል፤” ሕዝቡም ከተሞችን መሸገ፤ በለጸገም፤ 8ንጉሥ አሳ ታላላቅ ጋሻና ጦር የታጠቁ ሦስት መቶ ሺህ ሠራዊት ከይሁዳ፥ ታናናሽ ጋሻና ቀስት የያዙ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሺህ ሠራዊት ከብንያም ነበሩት፤ እነዚህ ሁሉ በሚገባ የሠለጠኑ ጀግኖች ወታደሮች ነበሩ።
9ዜራሕ ተብሎ የሚጠራ ኢትዮጵያዊ አንድ ሚሊዮን ወታደሮችና ሦስት መቶ ሠረገሎች ይዞ ይሁዳን ለመውረር እስከ ማሬሻ ገሥግሦ መጣ፤ 10አሳም ጦርነት ሊገጥመው ወጣ፤ ሁለቱም ወገኖች ማሬሻ አጠገብ በሚገኘው በጸፋታ ሸለቆ ቦታ ቦታቸውን በመያዝ ለውጊያ ተዘጋጁ፤ 11በዚህ ጊዜ አሳ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፥ ኀያላኑንም ሠራዊት ሆነ ደካማውንም የመርዳት ችሎታ አለህ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ በአንተ ስለ ተማመንን እነሆ፥ ይህን ብዙ ሠራዊት ለመውጋት መጥተናልና እባክህ እርዳን፤ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ አምላካችን ነህ፤ አንተን ማሸነፍ የሚችል ማንም የለም።”
12እግዚአብሔርም ኢትዮጵያውያንን እንዲያሸንፉ ዓሣንና ሠራዊቱን ረዳቸው፤ ኢትዮጵያውያንም ሸሹ። 13አሳና ሠራዊቱም እስከ ገራር ድረስ አሳደዱአቸው፤ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ብዙ ሰዎች ስላለቁ፥ ሠራዊቱ እንደገና ተንሠራርቶ ሊዋጋ አልቻለም፤ በዚህም ዐይነት ኢትዮጵያውያን በእግዚአብሔርና በሠራዊቱ ድል ሆኑ፤ የይሁዳ ሰዎችም እጅግ የበዛ ምርኮ ወሰዱ፤ #14፥13 ብዙ ሰዎች ስላለቁ ሠራዊቱ እንደገና ተንሠራርቶ ሊዋጋ አልቻለም፦ ወይም ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ወደቁ። 14በዚያ አካባቢ የነበሩ ሕዝቦች እግዚአብሔር ባደረገው ነገር እጅግ ተሸብረው ነበር፤ የአሳም ወታደሮች በገራር ዙሪያ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ ደመሰሱ፤ ከተሞቹንም ሁሉ በመዝረፍ ብዙ ምርኮ ወሰዱ፤ 15እንዲሁም በአንዳንድ እረኞች ሰፈር ላይ አደጋ በመጣል ብዙ በጎችን፥ ፍየሎችንና ግመሎችን ማረኩ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ