የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 10

10
በሰሜናዊ ግዛት የሚኖሩ የእስራኤል ነገዶች ማመፅ
(1ነገ. 12፥1-20)
1ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ፤ በዚያም እርሱን ለማንገሥ የፈለጉ በእስራኤል ሰሜናዊ ግዛት የሚኖሩ እስራኤላውያን ተሰብስበው ይጠብቁት ነበር፤ 2ከንጉሥ ሰሎሞን በመሸሽ ወደ ግብጽ ኮብልሎ የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን ወሬ በሰማ ጊዜ ከግብጽ ተመልሶ ወደ አገሩ ወደ እስራኤል መጣ፤ 3እርሱንም በእስራኤል ሰሜናዊ ግዛት የሚኖሩ ነገዶች መልእክት ልከው አስጠሩት፤ ከእርሱም ጋር አብረው ወደ ሮብዓም በመቅረብ፥ 4“አባትህ ሰሎሞን በእኛ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖ አስጨንቆን ነበር፤ ከችግራችን ብታወጣን እንገዛልሃለን” አሉት።
5ሮብዓምም “እኔም በጒዳዩ እንዳስብበት ጊዜ ስጡኝ፤ ከሦስት ቀን በኋላም ተመልሳችሁ ኑ” አላቸው፤ ስለዚህ እነርሱም ተመልሰው ሄዱ።
6ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሮብዓም የአባቱ የሰሎሞን አማካሪዎች የነበሩትን ሽማግሌዎች በአንድነት ሰብስቦ “እንግዲህ ለዚህ ሕዝብ መልስ መስጠት እንድችል ምን ትመክሩኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
7ሽማግሌዎቹም “ለእነርሱ ደግነትን ብታሳያቸው፥ ለጥያቄአቸውም ተስማሚ የሆነ መልስ በመስጠት ደስ ብታሰኛቸው፥ እነርሱ ዘወትር በታማኝነት ያገለግሉሃል” ሲሉ መለሱለት።
8ሮብዓም ግን የሽማግሌዎቹን ምክር ቸል በማለት ቀድሞ አብሮ ዐደጎቹና አገልጋዮቹ የነበሩትን ጠርቶ፥ 9“ላደርገው ስለሚገባኝ ነገር ምን ትመክሩኛላችሁ? የአገዛዝ ቀንበር እንዳቀልላቸው ለጠየቁኝስ ሰዎች ምን መልስ ልስጣቸው?” ሲል ጠየቃቸው።
10እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “አባትህ ቀንበር አክዶብን ነበር፤ አንተ ግን አቅልልልን ለሚሉህ ሰዎች የምትሰጣቸው መልስ ይህ ነው፦ ‘የእኔ ታናሽ ጣት ከአባቴ ወገብ ይበልጥ ትወፍራለች፤ 11አባቴ በእናንተ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ደግሞ ይኸው የአገዛዝ ቀንበር ይበልጥ እንዲከብድባችሁ አደርጋለሁ፤ ይኸውም አባቴ በአለንጋ ይገርፋችሁ ነበር፤ እኔ ግን እንደ ጊንጥ በሚናደፍ ጅራፍ በመግረፍ አሠቃያችኋለሁ።’ ”
12ከሦስት ቀን በኋላ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ ሮብዓም በሰጣቸው ቀጠሮ መሠረት ተመልሰው ወደ እርሱ መጡ። 13ንጉሥ ሮብዓምም ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ውድቅ አድርጎ ሕዝቡን በማመናጨቅ መናገር ጀመረ፤ 14ወጣቶቹም በሰጡት ምክር መሠረት “አባቴ በእናንተ ላይ ከባድ የአገዛዝ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ደግሞ ይኸው የአገዛዝ ቀንበር ይበልጥ እንዲከብድባችሁ አደርጋለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ይገርፋችሁ ነበር፤ እኔ ግን እንደ ጊንጥ በሚናደፍ ጅራፍ በመግረፍ አሠቃያችኋለሁ!” ሲል መለሰላቸው። 15ይህም የሆነበት ምክንያት ከሴሎ በመጣው በነቢዩ አኪያ አማካይነት ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም እግዚአብሔር የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው፤ ንጉሥ ሮብዓምም የሕዝቡን ሐሳብ ችላ በማለት ሳይቀበል የቀረበትም ምክንያት ይኸው ነው።
16እስራኤላውያን ንጉሥ ሮብዓም ጥያቄአቸውን እንዳልተቀበላቸው በተገነዘቡ ጊዜ፥ “ከዳዊት ጋር ምን ድርሻ አለን? ከእሴይ ልጅስ ጋር ምን ግንኙነት አለን? እስራኤል ሆይ! ወደ እየቤትህ ሂድ! ዳዊት ሆይ የራስህን ቤት ጠብቅ!” ብለው መለሱለት። ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ወደ የቤቱ ሄደ። #2ሳሙ. 20፥1።
17ሮብዓምም በይሁዳ ግዛት በሚኖር ሕዝብ ላይ ብቻ ነገሠ።
18ከዚህም በኋላ ንጉሥ ሮብዓም የጒልበት ሥራ የሚሠሩ ገባሮች ኀላፊ የነበረውን አዶኒራምን ወደ እስራኤላውያን እንዲሄድ ላከው፤ እነርሱ ግን በድንጋይ ወግረው ገደሉት፤ በዚህን ጊዜ ሮብዓም በፍጥነት ወደ ሠረገላው ገብቶ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ አመለጠ። 19ከዚያን ጊዜም ጀምሮ ሰሜናዊው ክፍል እስራኤል በሚል ስም በዳዊት ሥርወ መንግሥት ላይ ዐመፀ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ