1 ወደ ጢሞቴዎስ 6:11-21

1 ወደ ጢሞቴዎስ 6:11-21 አማ05

የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! አንተ ግን ከዚህ ሁሉ ሽሽ፤ ጽድቅን፥ መንፈሳዊነትን፥ እምነትን፥ ፍቅርን፥ በትዕግሥት መጽናትን፥ ገርነትን ተከታተል። የእምነትን መልካም ጦርነት ተዋጋ፤ አንተ ወደ እርሱ በተጠራህ ጊዜ በብዙ ምስክሮች ፊት ትክክለኛ ምስክርነትን የሰጠኸውን ዘለዓለማዊውን ሕይወት ያዝ። ለሁሉ ነገር ሕይወት በሚሰጠው በእግዚአብሔርና በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት በመልካም መታመን በመሰከረው በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት አዝሃለሁ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከሚገለጥበት ቀን ድረስ ይህን ትእዛዝ ያለ ስሕተትና ያለ ነቀፋ ጠብቅ። የክርስቶስም መገለጥ፥ የተባረከና፥ ብቻውን ገዢ የሆነ፥ የነገሥታት ንጉሥ፥ የጌቶች ጌታ በወሰነው ቀን ይሆናል፤ እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ እርሱን ከቶ ማንም አላየውም፤ ማንም ሊያየውም አይችልም፤ ክብርና ዘለዓለማዊ ኀይል ለእርሱ ይሁን፤ አሜን። የዚህ ዓለም ሀብታሞች እንዳይታበዩ ወይም ተስፋቸውን አስተማማኝ ባልሆነ ሀብት ላይ እንዳያደርጉ እዘዛቸው፤ እንዲሁም ተስፋቸው እኛን ደስ እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር ላይ እንዲሆን እዘዛቸው። ደግሞም መልካም ሥራ እንዲሠሩ፥ በመልካም ሥራ ሀብታሞች እንዲሆኑ፥ ለመለገሥና ያላቸውንም ለማካፈል ዝግጁዎች እንዲሆኑ እዘዛቸው። በዚህ ዐይነት እውነተኛውን ሕይወት ለማግኘት መሠረቱ ጽኑ የሆነውን ሀብት በሚመጣው ዘመን ለራሳቸው ያከማቻሉ። ጢሞቴዎስ ሆይ! በዐደራ የተሰጠህን ጠብቅ፤ ዕውቀት ሳይሆን “ዕውቀት” ከሚመስለው ነገር ልፍለፋ ራቅ። አንዳንዶች እንዲህ ዐይነቱ ዕውቀት አለን በማለት ከእምነት መንገድ ወጥተዋል። የእግዚአብሔር ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።