1 ወደ ጢሞቴዎስ 2:8-15

1 ወደ ጢሞቴዎስ 2:8-15 አማ05

እንግዲህ በየስፍራው ያሉ ወንዶች ቊጣንና ጥልን አስወግደው የተቀደሱ እጆቻቸውን ወደ ላይ በማንሣት እንዲጸልዩ እፈልጋለሁ። እንዲሁም ሴቶች ጠጒርን በማሳመር ወይም በወርቅ ወይም በዕንቊ ወይም ውድ በሆነ ልብስ በማጌጥ ሳይሆን በማፈርና በትሕትና ተገቢ የሆነ የጨዋ ልብስ ይልበሱ። እግዚአብሔርን እናመልካለን የሚሉ ሴቶች ማድረግ በሚገባቸው ዐይነት በመልካም ሥራ ያጊጡ። ሴት በጸጥታና በመታዘዝ ትማር፤ ሴት ወንድን እንድታስተምር ወይም በወንድ ላይ ሥልጣን እንዲኖራት አልፈቅድም፤ እርስዋ ዝም ማለት ይገባታል። በመጀመሪያ የተፈጠረ አዳም ነው፤ በኋላም ሔዋን ተፈጠረች። ደግሞም የተታለለችውና የእግዚአብሔርን ሕግ ያፈረሰችው ሴት ናት እንጂ የተታለለው አዳም አይደለም። ነገር ግን ሴት በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ብትጽናና ራስን በመቈጣጠር ብትኖር ልጅ በመውለድ ትድናለች።