ወንድሞች ሆይ! የእኛ ወደ እናንተ መምጣት ፍሬቢስ እንዳልሆነ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። እናንተ እንደምታውቁት ከዚህ ቀደም በፊልጵስዩስ በነበርንበት ጊዜ መከራና ስድብ ደርሶብናል፤ ነገር ግን ታላቅ ተቃውሞ ቢደርስብንም እንኳ ወንጌሉን ለእናንተ እንድናስተምር አምላካችን ድፍረትን ሰጥቶናል። እኛ የመከርናችሁ በስሕተት ወይም በርኩስ ዓላማ ተመርተን አይደለም፤ እናንተን ለማታለል ያደረግነው ምንም ነገር የለም። ይልቅስ እግዚአብሔር ወንጌሉን ለእኛ በዐደራ የሰጠን በእኛ ተማምኖ ስለ ሆነ እንናገራለን፤ ይህንንም የምናደርገው ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ብለን ነው እንጂ ሰውን ለማስደሰት ብለን አይደለም። አንድም ጊዜ በቃላት በማቈላመጥ ወይም የገንዘብ ፍላጎት ኖሮን ከቶ እንዳልተናገርን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ እግዚአብሔርም ምስክራችን ነው። ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ከማንም ሰው ክብርን አልፈለግንም። የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን አስፈላጊውን ከእናንተ ለመጠየቅ እንችል ነበር፤ ነገር ግን ለልጆችዋ እንደምትጠነቀቅ እናት በገርነት በመካከላችሁ ተመላለስን። እንዲሁም በጣም ስለምንወዳችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ማብሠር ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንንም እንኳ ልንሰጣችሁ ዝግጁዎች ነበርን። ወንድሞች ሆይ! እንዴት እንደ ሠራንና እንደ ደከምን ታውቃላችሁ፤ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ በምናበሥርበት ጊዜ በአንዳችሁም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን በመሥራት እንደክም ነበር። በእናንተ በአማኞች መካከል በነበርንበት ጊዜ እንዴት ባለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ሕይወት እንደ ኖርን እናንተ ምስክሮች ናችሁ፤ እግዚአብሔርም ምስክር ነው፤ አባት ለልጆቹ እንደሚያደርገው ዐይነት እኛም ለእናንተ ለእያንዳንዳችሁ እንዳደረግንላችሁ ታውቃላችሁ፤ ዘወትር እየመከርናችሁና እያበረታታናችሁ መንግሥቱንና ክብሩን እንድትካፈሉ የጠራችሁ አምላክ ደስ በሚሰኝበት ሁኔታ እንድትኖሩ ዐደራ እንዳልናችሁ ታውቃላችሁ።
1 ተሰሎንቄ ሰዎች 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ተሰሎንቄ ሰዎች 2:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች