1 ተሰሎንቄ ሰዎች 1:1-10

1 ተሰሎንቄ ሰዎች 1:1-10 አማ05

የእግዚአብሔር አብና የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወገኖች ለሆኑ ለተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን፥ ከጳውሎስ፥ ከሲላስና ከጢሞቴዎስ የተላከ መልእክት ነው፤ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። እኛ ሁልጊዜ እናንተን በጸሎታችን እያስታወስን ለእግዚአብሔር ምስጋና እናቀርባለን። በአምላካችንና በአባታችን ፊት እምነታችሁ የሚሠራውን፥ ለፍቅር የምታደርጉትንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን ተስፋ በትዕግሥት መጠባበቃችሁን ሳናቋርጥ እናስታውሳለን። በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንደ መረጣችሁ እናውቃለን። ወንጌላችንን ያበሠርንላችሁ በቃል ብቻ ሳይሆን በኀይልና በመንፈስ ቅዱስ፥ ስለ ወንጌልም እውነት እርግጠኞች በመሆን ነው፤ ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ ለእናንተ ስንል እንዴት እንደ ኖርን ታውቃላችሁ። ብዙ መከራ ቢደርስባችሁም እንኳ ከመንፈስ ቅዱስ በተገኘ ደስታ አማካይነት ቃሉን ተቀብላችሁ የእኛንና የጌታ ኢየሱስን አርአያ የምትከተሉ ሆናችኋል። ስለዚህ በመቄዶንያና በአካይያ ለሚገኙት ምእመናን ሁሉ መልካም ምሳሌ ሆናችኋል። የጌታ ቃል ከእናንተ ወጥቶ የተሰማው በመቄዶንያና በአካይያ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ያላችሁ እምነት በሁሉ ቦታ ታውቆ ነበር፤ በዚህ ምክንያት እኛ ስለዚህ ጉዳይ ምንም መናገር አያስፈልገንም። ወደ እናንተ በመጣን ጊዜ እንዴት እንደ ተቀበላችሁን ሕያውና እውነተኛውን አምላክ ለማገልገል ከጣዖቶች ተለይታችሁ ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንደ ተመለሳችሁ እነዚያ ሰዎች ራሳቸው ይመሰክራሉ። እንዲሁም እግዚአብሔር ከሞት ያስነሣውን፥ ከሚመጣው ቊጣ የሚያድነንን፥ የልጁን የኢየሱስን ከሰማይ መምጣት እንዴት እንደምትጠባበቁም ይመሰክራሉ።