የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7:1-17

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7:1-17 አማ05

የቂርያትይዓሪም ሰዎችም የእግዚአብሔርን ታቦት ወስደው በኮረብታ ላይ ወደሚኖረው አቢናዳብ ተብሎ ወደሚጠራ ሰው ቤት አስገቡት፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት እንዲጠብቅ ልጁን አልዓዛርን የተለየ እንዲሆን አደረጉ። የእግዚአብሔር ታቦት ለረዥም ጊዜ በቂርያትይዓሪም ኖረ፤ ይኸውም ኻያ ዓመት ያኽል ነበር፤ በዚህን ጊዜ እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር እጅግ አለቀሱ። ሳሙኤልም የእስራኤልን ሕዝብ፦ “በሙሉ ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሳችሁ ባዕዳን አማልክትንና ዐስታሮትን ከእናንተ ዘንድ አስወግዱ፤ ራሳችሁንም ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ እግዚአብሔርም ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድናችኋል” አላቸው። ስለዚህም እስራኤላውያን የባዓልንና የዐስታሮትን ጣዖቶች አስወግደው እግዚአብሔርን ብቻ አመለኩ። ከዚህም በኋላ ሳሙኤል “እኔ በዚያ ለእናንተ ወደ እግዚአብሔር ስለምጸልይላችሁ በምጽጳ ተሰብሰቡ” ብሎ ለእስራኤላውያን ሁሉ ጥሪ አደረገ። እነርሱም በአንድነት በምጽጳ ተሰበሰቡ፤ ውሃም ቀድተው ለእግዚአብሔር መባ አድርገው በማፍሰስ በዚያን ዕለት ቀኑን ሙሉ ጾሙ፤ “እኛ እግዚአብሔርን በድለናል” ብለውም ተናዘዙ፤ ሳሙኤል በእስራኤላውያን መካከል ይፈርድ የነበረው በምጽጳ ነበር። እስራኤላውያን በምጽጳ መሰብሰባቸውንም ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ አምስቱ የፍልስጥኤም ገዢዎች አደጋ ሊጥሉባቸው ወጡ፤ እስራኤላውያንም ይህን በሰሙ ጊዜ ፈሩ። ሳሙኤልንም፦ “ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድነን ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር መጸለይን አታቋርጥ” አሉት። ሳሙኤልም ገና ጡት ያልተወ ትንሽ የበግ ጠቦት ዐርዶ በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ ለእግዚአብሔር አቀረበው፤ ከዚህም በኋላ ስለ እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰማለት፤ ሳሙኤል የሚቃጠለውን መሥዋዕት በማቅረብ ላይ ሳለ ፍልስጥኤማውያን እስራኤላውያንን ለመውጋት ዘመቱ፤ ነገር ግን በዚያች ቀን እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ላይ ከፍተኛ ነጐድጓድ አንጐድጒዶ አርበደበዳቸው፤ እነርሱም ከእስራኤላውያን ፊት ሸሹ። እስራኤላውያንም ከምጽጳ ተነሥተው ፍልስጥኤማውያንን እስከ ቤትካር በታች እያሳደዱ በየመንገዱ ገደሉአቸው። ሳሙኤልም አንድ ድንጋይ ወስዶ በምጽጳና በሼን መካከል ተከለው፦ እግዚአብሔር እስካሁን ረድቶናል ለማለት ስሙን አቤንዔዜር ብሎ ሰየመው። በዚህም ዐይነት ፍልስጥኤማውያን ድል ተመቱ። ሳሙኤል በኖረበት ዘመን ሁሉ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ስለ ነበረ ፍልስጥኤማውያን ዳግመኛ ወደ እስራኤል ድንበር አልቀረቡም። ፍልስጥኤማውያን የያዙአቸው በዔቅሮንና በጋት መካከል የነበሩትም ከተሞች ሁሉ ለእስራኤላውያን ተመለሱላቸው፤ እስራኤላውያንም ድንበሮቻቸውን ከፍልስጥኤማውያን እጅ አዳኑ፤ በእስራኤላውያንና በአሞራውያን መካከልም ዕርቀ ሰላም ወርዶ ነበር። ሳሙኤል በነበረበት ዘመን ሁሉ የእስራኤልን ሕዝብ መራ፤ በየዓመቱም ወደ ቤትኤል፥ ጌልጌላና ምጽጳ እየሄደ በእነዚህ ስፍራዎች ይፈርድ ነበር። ከዚያም በራማ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ እየተመለሰ እዚያም የዳኝነት ሥራ ይሠራ ነበር፤ በዚህም በራማ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።