የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት በፍልስጥኤም ሰባት ወር ከቈየ በኋላ፥ ሕዝቡ ካህናታቸውንና አስማተኞቻቸውን ጠርተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁአቸው፤ “ስለ እግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ምን ማድረግ የሚሻለን ይመስላችኋል? ወደ ስፍራው እንዲመለስ ብናደርግ በምን ሁኔታ እንላከው? ዘዴውን ንገሩን” አሉአቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ “የእስራኤልን አምላክ የቃል ኪዳን ታቦት መልሳችሁ ለመላክ ብትፈልጉ፥ ስለ በደላችሁ የሚከፈል ስጦታ አብራችሁ መላክ ይገባችኋል፤ የቃል ኪዳኑ ታቦት ያለ ምንም ስጦታ ተመልሶ መሄድ የለበትም፤ በዚህም ዐይነት እናንተ ከሕመማችሁ ትፈወሳላችሁ፤ እርሱ እናንተን በብርቱ የቀጣበትንም ምክንያት ልታውቁ ትችላላችሁ።” ሕዝቡም፥ “ስለ በደል የሚከፈል ይሆን ዘንድ ከምን ዐይነት ስጦታ ጋር እንላከው?” ሲሉ ጠየቁ። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፦ “በእባጩ አምሳል የተሠራ አምስት የወርቅ ጒልቻ፥ እንደ ፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ብዛት በአይጥ አምሳል የተሠራ አምስት የወርቅ ጉልቻ መሆን አለበት፤ በእናንተ ሁሉና በአምስቱ ገዢዎች ላይ የተላከው መቅሠፍት አንድ ዐይነት ነው። አገራችሁን ለማጥፋት በተላኩት አይጦችና እባጮች አምሳል እነዚህን ስጦታዎች ሠርታችሁ ለእስራኤል አምላክ ክብር መስጠት አለባችሁ፤ ይህን ብታደርጉ ምናልባት እናንተን፥ አማልክታችሁንና ምድራችሁን የሚቀጣበትን መቅሠፍት ያነሣ ይሆናል፤ የግብጽ ንጉሥና ግብጻውያን እንዳደረጉት ስለምን ልባችሁን ታደነድናላችሁ? እስራኤላውያን የግብጽን ምድር ለቀው የወጡት፥ እግዚአብሔር ግብጻውያንን በብርቱ ከቀጣቸው በኋላ አልነበረምን? ስለዚህ አዲስ ሠረገላና ቀንበር ያልተጫነባቸው ሁለት ጥጆችን አዘጋጁ፤ ጥጆቹን ጠምዳችሁ ሠረገላው የሚሳብበትን ጫፍ በቀንበሩ ላይ እሰሩት፤ እንቦሶቻቸውንም ወደ በረት መልሱ፤ የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳን ታቦት ወስዳችሁ በሠረገላው ላይ አኑሩ፤ ስለ በደላችሁም እንዲከፈል ከእርሱ ጋር ለመላክ የሠራችሁትን ልዩ ልዩ ወርቅ በሣጥን ውስጥ አስገብታችሁ በታቦቱ ጐን አስቀምጡ፤ ሠረገላውንም መንገድ አስይዛችሁ እንዲንቀሳቀስ ተዉት። ከዚህም በኋላ አካሄዱን ተመልከቱት፤ አቅጣጫው ወደ ቤትሼሜሽ ከተማ ያመራ እንደ ሆነ ይህን አሠቃቂ መቅሠፍት በእኛ ላይ የላከብን እግዚአብሔር መሆኑን ያመለክታል፤ ወደዚያ አቅጣጫ ባያመራ ግን መቅሠፍቱ የመጣብን በአጋጣሚ እንጂ እግዚአብሔር የላከብን አለመሆኑን እንገነዘባለን።” እነርሱም እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ ሁለት ላሞች ወስደው ሠረገላ በታሰረበት ቀንበር ጠመዱአቸው፤ እንቦሶቻቸውንም ወደ በረት መልሰው ዘጉባቸው። የእግዚአብሔርንም ታቦት ወስደው በአይጦችና በእባጮች አምሳል የተሠራ ወርቅ ከተሞላበት ሣጥን ጋር በሠረገላው ላይ አስቀመጡ፤ ላሞቹም መንገዱን ሳይለቁና ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳያዘነብሉ በቀጥታ ወደ ቤትሼሜሽ በማምራት ጒዞአቸውን ቀጠሉ፤ በሚሄዱበትም ጊዜ እምቧ ይሉ ነበር፤ አምስቱ የፍልስጤማውያን ገዢዎችም እስከ ቤትሼሜሽ ድንበር ድረስ በመከተል ሸኙአቸው። የቤትሼሜሽም ሰዎች በሸለቆው ውስጥ ስንዴ ያጭዱ ነበር፤ ቀና ብለው በተመለከቱም ጊዜ ታቦቱን አዩ፤ ያንንም በማየታቸው እጅግ ደስ አላቸው። ሠረገላውም በቤትሼሜሽ ወደሚኖር ኢያሱ ተብሎ ወደሚጠራው ሰው እርሻ መጥቶ በትልቅ ቋጥኝ አጠገብ ሲደርስ ቆመ። ሕዝቡም የሠረገላውን እንጨት ፈለጡ፤ ላሞቹንም ዐርደው ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡአቸው። ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ታቦትና ከእርሱ ጋር የነበረውን ወርቅ የሞላበት ሣጥን አንሥተው በታላቁ ቋጥኝ ላይ አስቀመጡ፤ የቤትሼሜሽም ሰዎች የሚቃጠልና ሌላውንም መሥዋዕት ሁሉ ለእግዚአብሔር አቀረቡ፤ አምስቱም የፍልስጥኤም ገዢዎች ይህን ሁሉ ሲመለከቱ ቈይተው በዚያው ቀን ወደ ዔቅሮን ተመለሱ። ስለ በደላቸው የሚከፈሉ ስጦታዎች ይሆኑ ዘንድ ፍልስጥኤማውያን ለእግዚአብሔር የላኩአቸው በእባጮች አምሳል የተሠሩ አምስት የወርቅ እንክብሎች አሽዶድ፥ ጋዛ፥ አስቀሎና፥ ጋትና ዔቅሮን ተብለው በሚጠሩት ከተሞቻቸው ስም የተላኩ ነበሩ፤ እንዲሁም ከተላኩት መካከል በተመሸጉ ከተሞችና ቅጽር ባልተሠራላቸው መንደሮች ሆነው አምስቱ የፍልስጥኤም ገዢዎች በሚያስተዳድሩት በእያንዳንዱ ከተማ ስም በአይጥ አምሳል የተሠሩ አምስት የወርቅ እንክብሎች ነበሩ። በቤትሼሜሽ በሚኖረው በኢያሱ እርሻ ውስጥ የእግዚአብሔርን ታቦት ያኖሩበትም ታላቅ ቋጥኝ እስከ ዛሬ ድረስ ምስክር ሆኖ ይታያል። የታቦቱን ውስጣዊ ክፍል በመመልከታቸው እግዚአብሔር ተቈጥቶ ከቤት ሼሜሽ ሰዎች መካከል ሰባ ሰዎችን ገደለ፤ እግዚአብሔርም ይህን ሁሉ እልቂት በመካከላቸው በማድረጉ የቤት ሼሜስ ሰዎች በማዘን አለቀሱ።
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 6 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 6:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos