አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 31
31
የሳኦልና የልጆቹ አሟሟት
(1ዜ.መ. 10፥1-12)
1ፍልስጥኤማውያን በጊልቦዓ ተራራ ከእስራኤላውያን ጋር ጦርነት ገጠሙ፤ ብዙ እስራኤላውያንም ሸሹ፤ ብዙዎችም ተገደሉ። 2ፍልስጥኤማውያን ግን ተከታትለው ስለ ደረሱባቸው ሦስቱን የሳኦልን ልጆች ዮናታንን፥ አቢናዳብንና ማልኪሹዓን ገደሉአቸው። 3ጦርነቱ በሳኦል ዙሪያ ስለ በረታ ቀስተኞች ሳኦልን አገኙት፤ ወግተውም በጣም አቈሰሉት፤ 4ጋሻጃግሬው የነበረውንም ወጣት “እነዚህ ያልተገረዙ እኔን ወግተው በመሳለቅ መጫወቻ እንዳያደርጉኝ አንተ ራስህ ሰይፍህን መዘህ ግደለኝ” አለው፤ ወጣቱ ግን ፈርቶ አልገደለውም፤ ስለዚህም ሳኦል ራሱ የገዛ ሰይፉን ወስዶ በስለቱ ላይ ወደቀበት። 5ወጣቱም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱም በበኩሉ በራሱ ሰይፍ ስለት ላይ ወድቆ ከሳኦል ጋር ሞተ። 6እንግዲህ ሳኦልና ሦስቱ ወንዶች ልጆቹ እንዲሁም ጋሻጃግሬው የሞቱት በዚህ ዐይነት ሲሆን፥ የሳኦልም ተከታዮች በዚያን ቀን አብረዋቸው ሞቱ። 7ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅና በኢይዝራኤል ሸለቆ ማዶ የነበሩ እስራኤላውያንም የእስራኤል ሠራዊት መሸሹን፥ ሳኦልና ልጆቹም መገደላቸውን ሰምተው ከተሞቻቸውን እየጣሉ ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ከተሞቹን ያዙ።
8ከጦርነቱ ቀጥሎ ባለው ቀን ፍልስጥኤማውያን የሟቾቹን ሬሳ ትጥቅ ለመግፈፍ ሄደው ሳኦልንና ሦስቱን ልጆቹን በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው። 9የሳኦልንም ራስ ቈርጠው የጦር ልብሱንም ገፈው በማስያዝ ለአማልክቶቻቸው መቅደስና ለሕዝባቸው የድሉን ዜና ያበሥሩ ዘንድ መልእክተኞቻቸውን ላኩ። 10ከዚህ በኋላ ፍልስጥኤማውያን የሳኦልን የጦር መሣሪያዎች ዐስታሮት ተብላ በምትጠራው ሴት አምላካቸው ቤተ መቅደስ ውስጥ አኖሩ። የሳኦልንም ሬሳ ቤትሻን ተብላ በምትጠራው ከተማ ቅጽር ግንብ ላይ በምስማር ቸነከሩት።
11በገለዓድ የሚኖሩ የያቤሽ ሰዎችም ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉበትን ነገር በሰሙ ጊዜ፥ 12ጀግኖቻቸው በድንገት ተነሥተው በመገሥገሥ በሌሊት ወደ ቤትሻን ሄዱ፤ የሳኦልንና የልጆቹን አስከሬን ከከተማይቱ ቅጽር ግንብ ላይ አውርደው ወደ ያቤሽ በማምጣት አቃጠሉአቸው። 13አጥንቶቻቸውንም በከተማው ውስጥ ታማሪስክ ተብሎ በሚጠራ ዛፍ ሥር ቀብረው ሰባት ቀን ጾሙ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 31: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997