የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 28

28
1ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመውጋት የጦር ሠራዊታቸውን ሰበሰቡ፤ አኪሽም ዳዊትን “አንተና ተከታዮችህ ከእኔ ጐን ተሰልፋችሁ መዋጋት እንደሚገባችሁ በእርግጥ ዕወቅ” አለው።
2ዳዊትም “እኔ አገልጋይህ ነኝ፤ የማደርገውንም አንተ ራስህ ማየት ትችላለህ” ሲል መለሰለት።
አኪሽም “መልካም ነው! እኔ አንተን ለዘለቄታ የራሴ የክብር ዘብ አደርግሃለሁ!” አለው።
ሳኦል ከሙታን መናፍስት ጠሪ ምክር መጠየቁ
3እነሆ፥ ሳሙኤል ከሞተ ቈየት ብሎአል፤ እስራኤላውያንም ሁሉ ለእርሱ በማዘን አልቅሰው በሚኖርባት በራማ ቀብረውታል፤ ቀደም ሲል ሳኦል ጠንቋዮችንና ሙታን ጠሪዎችን ከእስራኤል ምድር እንዲባረሩ አስገድዶአቸው ነበር። #ዘሌ. 20፥27፤ ዘዳ. 18፥10-11፤ 1ሳሙ. 25፥1።
4የፍልስጥኤም ወታደሮች ተሰልፈው መጥተው በሹኔም ከተማ አጠገብ ሰፈሩ፤ ሳኦልም እስራኤላውያንን አሰልፎ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ሰፈረ፤ 5ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ብዛት ባየ ጊዜ ፈራ፤ ልቡም ተሸበረ፤ 6ስለዚህም ምን ማድረግ እንደሚገባው እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔር ግን በሕልም ወይም በኡሪም ወይም በነቢያት አማካይነት መልስ እንዲሰጠው አልፈቀደም። #ዘኍ. 27፥21። 7ከዚህ በኋላ ሳኦል “ሙታን ጠሪ የሆነች አንዲት ሴት ፈልጉልኝ፤ እኔም ሄጄ ምክር እጠይቃታለሁ” ሲል ባለሟሎቹን አዘዘ።
እነርሱም “አንዲት ዔንዶራዊት አለች” ሲሉ መለሱለት።
8ሳኦልም ልብሱን ለውጦ ማንነቱ እንዳይታወቅ በማድረግ በሌሊት ሁለት ሰዎች አስከትሎ ሴትዮዋን ለማየት ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሰ “መናፍስትን ጠይቀሽ ወደ ፊት ስለሚሆነው ነገር አስረጂኝ፤ ስሙንም የምጠራልሽን ሰው አስነሽልኝ” አላት።
9ሴትዮዋም “ንጉሥ ሳኦል ያደረገውን ነገር ሁሉ ታውቃለህ፤ እርሱ እኮ ጠንቋዮችንና ሙታን ጠሪዎችን ከእስራኤል ምድር አጥፍቶአቸዋል፤ ታዲያ አንተ እኔን አጥምደህ ልታስገድለኝ የምትፈልገው ስለምንድን ነው?” ስትል መለሰችለት።
10ከዚያም በኋላ ሳኦል “በዚህ ነገር ምንም ዐይነት ቅጣት እንደማይደርስብሽ በሕያው እግዚአብሔር ስም ምዬ ቃል እገባልሻለሁ” አላት።
11“ታዲያ ማንን ላስነሣልህ?” ስትል ጠየቀችው።
እርሱም “ሳሙኤልን አስነሽልኝ” አላት።
12እርስዋም ሳሙኤልን ባየችው ጊዜ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ በመጮኽ “ስለምን አታለልከኝ? አንተ ንጉሥ ሳኦል ነህ!” አለችው።
13ንጉሡም “አይዞሽ አትፍሪ! ይልቅስ የምታዪው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት።
እርስዋም “እኔ አንድ መለኮታዊ ግርማ ያለው ከመቃብር ሲወጣ እያየሁ ነኝ” አለችው።
14እርሱም “መልኩ ምንን ይመስላል?” ሲል ጠየቃት።
እርስዋም “እነሆ፥ ካባ የለበሰ አንድ ሽማግሌ ሰው እየተነሣ ነው” ስትል መለሰችለት።
ሳኦልም ያ ሳሙኤል መሆኑን ዐውቆ ስለ ክብሩ በመሬት ላይ ለጥ ብሎ እጅ ነሣ።
15ሳሙኤልም ሳኦልን “ዕረፍት የምትነሣኝ ስለምንድን ነው? ስለምንስ ከመቃብር እንድነሣ አስጠራኸኝ?” አለው።
ሳኦልም “እነሆ፥ እኔ በታላቅ ችግር ላይ ነኝ! ፍልስጥኤማውያን ከእኔ ጋር ጦርነት በማድረግ ላይ ናቸው፤ እግዚአብሔርም እኔን ትቶኛል፤ በነቢይም ሆነ በሕልም መልስ ሊሰጠኝ አልፈለገም፤ ስለዚህም ምን ማድረግ እንደሚገባኝ ትነግረኝ ዘንድ እንድትነሣ አስጠራሁህ” ሲል መለሰ።
16ሳሙኤልም ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር ተለይቶህ ጠላትህ ከሆነ በኋላ እኔን ስለምን ታስጠራኛለህ? 17እግዚአብሔር በእኔ አማካይነት የነገረህን ሁሉ እየፈጸመ ነው፤ መንግሥቱንም ከአንተ እጅ ወስዶ ለጐረቤትህ ለዳዊት ሰጥቶታል፤ #1ሳሙ. 15፥28። 18አንተ ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዥ ሆነህ አልተገኘህም፤ ዐማሌቃውያንና የእነርሱ የሆነውንም ሁሉ አልደመሰስክም፤ እንግዲህ እግዚአብሔር አሁን ይህን ሁሉ የሚያደርግብህ በዚህ ምክንያት ነው። #1ሳሙ. 15፥3-9። 19ስለዚህ እርሱ አንተንና እስራኤልን ለፍልስጥኤማውያን አሳልፎ ይሰጣችኋል፤ ነገ አንተና ልጆችህ እኔ ወዳለሁበት ቦታ ትመጣላችሁ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ሠራዊት ለፍልስጥኤማውያን አሳልፎ ይሰጣል።”
20ሳኦልም ሳሙኤል በተናገረው ቃል ደንግጦ በመዝለፍለፍ ወደቀ፤ በመሬት ላይም ተዘረረ፤ ቀኑንና ሌሊቱን ሁሉ እህል ስላልቀመሰ ድካም ተሰምቶት ነበር። 21ሴቲቱም ወደ ሳኦል መጥታ ሲንቀጠቀጥ ስላየችው እንዲህ አለችው፦ “እኔ አገልጋይህ የአንተን ቃል ሰምቼ ሕይወቴን እስከ ማሳለፍ ደርሼአለሁ፤ ያልከኝንም ነገር አዳመጥኩ፤ 22አንተ ደግሞ አሁን የእኔን የአገልጋይህን ቃል ስማ፤ ምግብ ላዘጋጅልህና ተመገብ መንገድህንም በርትተህ መሄድ ትችላለህ።”
23ሳኦል “ምንም ነገር አልቀምስም” ብሎ እምቢ አለ፤ ይሁን እንጂ ባለሟሎቹም እንዲመገብ አበረታቱት፤ በመጨረሻም “እሺ” ብሎ ከወደቀበት መሬት በመነሣት አልጋ ላይ ተቀመጠ፤ 24ሴትዮዋም የሰባ ጥጃ ነበራት እሱንም በፍጥነት ዐረደች፤ ጥቂት ዱቄትም ወስዳ በማቡካት እርሾ ያልነካው ቂጣ ጋገረች። 25ምግቡንም ለሳኦልና ለባለሟሎቹ አቅርባላቸው ተመገቡ፤ በዚያኑም ምሽት ከዚያ ተነሥተው ሄዱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ