አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 29
29
ፍልስጥኤማውያን ዳዊትን መቃወማቸው
1እስራኤላውያን በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ በሚገኘው ምንጭ አጠገብ ሰፍረው ሳሉ፥ ፍልስጥኤማውያን ወታደሮቻቸውን በአንድነት ሰብስበው በማምጣት በአፌቅ አሰለፉ፤ 2አምስቱም የፍልስጥኤም ነገሥታት በመቶና በሺህ ከተመደቡ ሰልፈኞቻቸው ጋር ዘመቱ፤ ዳዊትና ተከታዮቹም የአኪሽ ደጀን ጦር ሆነው ዘመቱ፤ 3የፍልስጥኤም ጦር አዛዦችም እነርሱን ባዩ ጊዜ “እነዚህ ዕብራውያን እዚህ ምን ይሠራሉ?” ሲሉ ጠየቁ።
አኪሽም “ይህማ የእስራኤል ንጉሥ ባለሟል የነበረው ዳዊት አይደለምን? እነሆ እርሱ ከእኔ ጋር ሲኖር ብዙ ጊዜው ነው፤ ሳኦልን ከድቶ ወደ እኔ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ሊያሳዝነኝ የሚችል ምንም ዐይነት በደል ሠርቶ አልተገኘም” ሲል መለሰ።
4ነገር ግን የፍልስጥኤም ጦር አዛዦች በአኪሽ ላይ ተቈጥተው እንዲህ አሉት፤ “ይህን ሰው ቀድሞ ወደ ሰጠኸው ከተማ መልሰው፤ ከእኛ ጋር አብሮ እንዲዘምት አታድርግ፤ ጦርነቱ በሚፋፋምበት ወቅት በእኛ ላይ ሊነሣ ይችላል፤ እርሱ ከጌታው ጋር ለመስማማት የእኛን ሰዎች ከመግደል ሌላ ምን አማራጭ ይኖረዋል? 5ከዚህስ በቀር ቀደም ሲል ሴቶች ‘ሳኦል ሺህ ገዳይ! ዳዊት ዐሥር ሺህ ገዳይ!’ ብለው እየጨፈሩ የዘፈኑለት ይኸው ዳዊት አይደለምን?” #1ሳሙ. 15፥3-9።
6ስለዚህም አኪሽ ዳዊትን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “አንተ ለእኔ ታማኝ ስለ መሆንህ በሕያው አምላክ ስም እምላለሁ፤ ወደዚህም ጦርነት ዘምተህ ብትዋጋ ደስ ባለኝ ነበር፤ ወደ እኔ ከመጣህበት ጊዜ ጀምሮ እኔን ማሳዘን የሚችል በደል ሠርተህ አላገኘሁህም፤ ነገር ግን ሌሎቹ ገዢዎች የአንተን አብሮ መዝመት አልፈቀዱም፤ 7አሁን እንግዲህ ወደ ኋላ ተመለስ፤ በሰላም ሂድ፤ የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ቅር የሚያሰኝ ምንም ነገር አታድርግ።”
8ዳዊትም “ጌታዬ ምን በደል ሠራሁ? አንተን ማገልገል ከጀመርኩበት ጊዜ አንሥቶ በደል ካልተገኘብኝ ጌታዬና ንጉሤ የሆንከውን አንተን ተከትዬ በመዝመት ጠላቶችህን መውጋት የማልችለው ስለምንድን ነው?” አለው።
9አኪሽም ዳዊትን መልሶ እንዲህ አለው፦ “አንተ በእኔ አስተያየት እንደ እግዚአብሔር መልአክ ምንም እንከን የሌለብህ መሆኑን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች ‘ከእኛ ጋር ወደ ጦርነት መዝመት አይችልም’ አሉ። 10ስለዚህ አንተና ከአንተ ጋር የመጡ የጌታህ አገልጋዮች ነገ ጠዋት ሲነጋጋ በመነሣት ወደ ሰፈራችሁ ተመለሱ” ሲል መለሰለት።
11ስለዚህም ዳዊትና ተከታዮቹ በማግስቱ ማለዳ ወደ ፍልስጥኤም ተመልሰው ለመሄድ ተነሡ፤ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ኢይዝራኤል ዘመቱ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 29: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997