አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 27
27
ዳዊት በፍልስጥኤማውያን መካከል
1ዳዊት በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፤ “አንድ ቀን ሳኦል እኔን ይገድለኛል፤ እንግዲህ ለእኔ የሚበጀኝ ነገር አምልጬ ወደ ፍልስጥኤም መሄድ ነው፤ ከዚያም በኋላ ሳኦል በእስራኤል ምድር እኔን መፈለጉን ስለሚተው ከእጁ አመልጣለሁ።” 2ስለዚህም ዳዊትና ስድስት መቶ ተከታዮቹ ወዲያውኑ ተነሥተው የጋት ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ ማዖክ ልጅ ወደ አኪሽ ሄዱ፤ 3ዳዊትና ተከታዮቹም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በጋት ተቀመጡ፤ ከዳዊትም ጋር ሁለቱ ሚስቶቹ አብረው ነበሩ፤ እነርሱም የኢይዝራኤል ተወላጅ የሆነችው አሒኖዓምና የቀርሜሎሱ ተወላጅ ናባል አግብቶአት የነበረው አቢጌል ነበሩ፤ 4ሳኦልም ዳዊት ወደ ጋት ሸሽቶ መሄዱን በሰማ ጊዜ እርሱን ፈልጎ ለማግኘት ያደርገው የነበረውን ሙከራ ሁሉ አቆመ።
5ዳዊትም ንጉሥ አኪሽን “የምትወደኝ ከሆንክ በአንድ ትንሽ ከተማ እንድኖር ፍቀድልኝ፤ ጌታዬ ሆይ፥ እኔ በመናገሻ ከተማ ከአንተ ጋር መኖር አይገባኝም” አለው። 6ስለዚህም አኪሽ የጺቅላግን ከተማ ለዳዊት ሰጠው፤ በዚህም ምክንያት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጺቅላግ የይሁዳ ነገሥታት ይዞታ እንደ ሆነች ቀረች። 7በዚህ ዐይነት ዳዊት በፍልስጥኤም አንድ ዓመት ከአራት ወር ተቀመጠ።
8በዚያን ጊዜ ውስጥ ዳዊትና ተከታዮቹ በጌሪሹራውያን፥ በጌዛውያንና በአማሌቃውያን ላይ ዘመቱ፤ እነዚህም አገሮች ከቴሌኦም ጀምሮ ወደ ሱርና ወደ ምድረ ግብጽ የሚወስዱ እነርሱ የሚኖሩባቸው አገሮች ነበሩ። 9ወንዶችንም ሴቶችንም ሁሉ እየገደለ፥ በጎችን የቀንድ ከብቶችን፥ አህዮችን፥ ግመሎችንና ልብሱንም ሁሉ ይወስድ ነበር፤ ከዚያም በኋላ ዳዊት ወደ አኪሽ ተመለሰ፤ 10አኪሽ “በዚህ ጊዜ ወረራ ያደረጋችኹት በየት በኩል ነው” ብሎ ሲጠይቀው ዳዊት “እኛ የዘመትነው ከይሁዳ በስተ ደቡብ ባለው ክፍል፥ እንደገናም በይራሕመኤል ነገድ ግዛትና ቄናውያን በሚኖሩበት ግዛት ነው” እያለ ይመልስለት ነበር። 11ዳዊት ወንድንም ሆነ ሴትን ወደ ጋት ሳያመጣ ሁሉንም ገደለ። ይህንንም ያደረገው ዳዊት ይህንንና ይህንን አደረገ ብለው እንዳይነግሩበት ነው። በፍልስጥኤም አገር በኖረበት ዘመን ሁሉ ይህን የማድረግ ልማድ ነበረው። 12አኪሽ ግን ዳዊትን ስለሚተማመንበት በልቡ “በወገኖቹ በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ የተጠላ ስለ ሆነ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ያገለግለኛል” በማለት ያስብ ነበር።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 27: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997