ሐናም እንዲህ ብላ ጸለየች፦ “ልቤ በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፤ ክብሬም በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ ብሎአል፤ በማዳንህ ስለ ተደሰትኩ፤ በጠላቶቼ ላይ እሳለቃለሁ። “እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለም፤ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ አምላካችንን የሚመስልም መጠጊያ ምሽግ የለም፤ እስቲ በመታበይ አትጓደዱ፤ የትምክሕት ንግግራችሁንም አስወግዱ፤ እግዚአብሔር አምላክ ሁሉን ያውቃል፤ ሕዝብ የሚሠራውንም ሁሉ በፍርድ ይመዝናል። የኀያላን ቀስቶች ተሰበሩ፤ ደካሞች ግን ብርታትን አግኝተው ጠነከሩ፤ ጠግበው የነበሩ ተርበው ለምግብ ተገዝተዋል፤ ተርበው የነበሩ ግን ጠግበዋል፤ መኻኒቱ ሰባት ወለደች፤ የብዙዎች ልጆች እናት የነበረችው ብቻዋን ቀረች። እግዚአብሔር ይገድላል፤ ያድናልም፤ ወደ ሲኦል ያወርዳል፤ ከሲኦልም ያወጣል፤ እግዚአብሔር ያደኸያል፤ ያበለጽጋልም፤ ያዋርዳል፤ ከፍ፥ ከፍም ያደርጋል። እርሱ ድኾችን ከትቢያ ምስኪኖችንም ከዐመድ ላይ ያነሣል፤ ወደ ልዑላንም ደረጃ ከፍ ያደርጋቸዋል፤ የክብርም ዙፋን ያወርሳቸዋል የምድርን መሠረቶች የሠራ እግዚአብሔር ነው፤ በእነርሱም ላይ ዓለምን የፈጠረ እርሱ ነው። “ሰው ድልን የሚያገኘው በኀይሉ ስላልሆነ እግዚአብሔር የታማኞቹን እርምጃዎች ይጠብቃል፤ ክፉዎች ግን ወደ ጨለማ ይጣላሉ። እግዚአብሔርን የሚቃወሙ ይደመሰሳሉ፤ ከሰማይም ያንጐደጒድባቸዋል፤ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ይፈርዳል፤ ለንጉሥም ኀይልን ይሰጠዋል፤ ለመረጠውም ክብሩን ከፍ ከፍ ያደርግለታል።” ከዚህ በኋላ ሕልቃና በራማ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ተመልሶ ሄደ፤ ሕፃኑ ሳሙኤልም በካህኑ ዔሊ ሥር ሆኖ እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር። የዔሊ ልጆች ምንም የማይረቡ ስድ አደጎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አያከብሩም ነበር፤ ካህናቱ ከሕዝቡ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንደዚህ ነበር፦ ሰው ሁሉ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ሥጋው በመብሰል ላይ እያለ የካህኑ አገልጋይ ሦስት ጣት ያለውን ሜንጦ ይዞ ይቀርብ ነበር። እርሱም ሜንጦውን ወደ ድስቱ፥ ወይም ወደ ምንቸቱ፥ ወይም ወደ አፍላሉ፥ ወይም ወደ ቶፋው ይከተው ነበር፤ ሜንጦው የሚያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለራሱ ይወስደው ነበር፤ ይህንንም ድርጊት ወደ ሴሎ በሚመጡት እስራኤላውያን ሁሉ ላይ ያደርጉት ነበር። ከዚህም በቀር ጮማው ከመቃጠሉ በፊት የካህኑ አገልጋይ መሥዋዕቱን ወደሚሠዋው ሰው መጥቶ “ካህኑ ያንተን የተቀቀለ ሥጋ ሳይሆን ጥሬ ሥጋ ስለሚፈልግ ለእርሱ እንድጠብስለት ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር። ሰውየውም “በመጀመሪያ ስቡን ያቃጥሉትና ከዚያ በኋላ የፈለግኸውን ትወስዳለህ” ቢለው፥ የካህኑ አገልጋይ “አይሆንም! አሁኑኑ ስጠኝ! እምቢ ብትል ግን በግድ እወስዳለሁ!” ይለው ነበር። በዚህም ዐይነት የእግዚአብሔርን መሥዋዕት ስላቃለሉ የዔሊ ልጆች ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ከፍተኛ ነበር። ሳሙኤል ግን ገና በልጅነቱ ከበፍታ የተሠራ ሸሚዝ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር፤ ይህም ቃል በዕብራይስጡ ካህኑ ለሚለብሰው ልብስ ወይም በደረቱ ላይ ስለሚያደርገው ነገር መጠሪያ ነው። እናቱም በየዓመቱ ባልዋን ተከትላ ዓመታዊውን መሥዋዕት ለማቅረብ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ ካባ እየሠራች ታመጣለት ነበር። ዔሊም ሕልቃናን ከሚስቱ ከሐና ጋር በሚመርቅበት ጊዜ፥ ሕልቃናን “ለእግዚአብሔር የተለየ አድርጋችሁ በሰጣችሁት በዚህ ልጅ ፈንታ ከዚህቹ ሴት ሌሎችን ልጆች ይስጥህ!” ይለው ነበር። ከዚያን በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር። እግዚአብሔርም ሐናን አስታወሳትና ሌሎች ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆችን ወለደች፤ ወጣቱ ሳሙኤልም እግዚአብሔርን እያገለገለ አደገ። እነሆ ዔሊ በዕድሜው አርጅቶ ነበር፤ ልጆቹም በእስራኤላውያን ላይ የሚያደርጉት ክፉ ነገርና በድንኳኑ ደጃፍ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደሚያመነዝሩ ሰማ። ስለዚህም እንዲህ አላቸው፤ “ስለምን ይህን ክፉ ነገር ታደርጋላችሁ? የምታደርጉትን ክፉ ነገር ሁሉ ከእያንዳንዱ ሰው ሰምቼዋለሁ፤ ልጆቼ ሆይ! በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ስለ እናንተ የተሠራጨው ወሬ መልካም አይደለምና እንዲህ ያለ ክፉ ነገር አታድርጉ! አንድ ሰው ሌላውን ሰው ቢበድል፥ እግዚአብሔር በመታደግ ሊያድነው ይችላል፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚበድል ሰው ማን ሊያማልደው ይችላል?” ሆኖም እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ቊርጥ ውሳኔ ስላደረገ የዔሊ ልጆች የአባታቸውን ምክር አልሰሙም። ወጣቱ ሳሙኤል ግን በቁመት እያደገ፥ በእግዚአብሔርና በሰውም ዘንድ ጸጋና ሞገስን እያገኘ ሄደ። ከእግዚአብሔር የተላከ አንድ ነቢይ ወደ ዔሊ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በፈርዖን ቤት ባሪያዎች በነበሩ ጊዜ ለቀድሞ አባትህ ለአሮን ራሴን ገለጥሁለት፤ እርሱንም ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ወደ መሠዊያዬ እንዲወጣ፥ እጣን እንዲያጥን፥ በፊቴ ኤፉድ እንዲለብስ፥ የእኔ ካህን ይሆን ዘንድ መረጥሁት፤ ለቀድሞ አባትህ ልጆችም የእስራኤል ልጆች የሚያቀርቡትን የሚቃጠል መሥዋዕት ሰጠኋቸው። በትእዛዜ መሠረት የሚቀርብልኝን መሥዋዕትና ቊርባን ለምን ታዋርዳላችሁ? ልጆችህ ለመሥዋዕት ከሚቀርበው ምርጥ የሆነውን እየወሰዱ በመብላት ይወፍሩ ዘንድ እነርሱን ከእኔ ይበልጥ የምታከብራቸው ለምንድነው?’
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2:1-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች