አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 18
18
1ሳኦልና ዳዊት ንግግራቸውን ከጨረሱ በኋላ የሳኦል ልጅ ዮናታን ከዳዊት ጋር እጅግ የተቀራረበ አንድነት መሠረተ፤ እንደ ራሱም አድርጎ ወደደው፤ 2ከዚያን ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ከእርሱ ጋር እንዲኖር አደረገ፤ ወደ ቤቱም እንዲሄድ አላሰናበተውም፤ 3ዮናታን ዳዊትን እንደ ራሱ አድርጎ ስለ ወደደው ከእርሱ ጋር የወዳጅነት ቃል ኪዳን ገባ፤ 4የለበሰውንም ካባ አውልቆ ለዳዊት ሰጠው፤ እንዲሁም የጦር ልብሱን፥ ሰይፉን፥ ቀስቱንና መታጠቂያውን ጭምር ሰጠው። 5ሳኦል በትእዛዝ በሚያዘምትበት ቦታ ሁሉ የዳዊት ተልእኮ የተሳካ ሆነ፤ ስለዚህም ሳኦል በጦር ሠራዊቱ ውስጥ የመኰንንነት ማዕርግ እንዲኖረው አደረገ፤ ይህም የሳኦልን የጦር መኰንኖችና ወታደሮችን ሁሉ አስደሰተ።
ሳኦል በዳዊት ላይ ምቀኝነትና ቅንአት እንዳደረበት
6ዳዊት ጎልያድን ገድሎ ሲመለስና ወታደሮችም ወደየቤታቸው በማምራት ላይ ሳሉ፥ በእስራኤል በሚገኙት ከተሞች ሁሉ የሚኖሩ ሴቶች ሳኦልን ለመቀበል ወጡ፤ እነርሱም በእልልታ እየዘፈኑና እየጨፈሩ፥ የመስንቆ ድምፅ እያሰሙ አታሞ ይመቱ ነበር። 7ሴቶቹም ባደረጉት የአቀባበል ሥርዓት ላይ “ሳኦል ሺህ ገዳይ! ዳዊት ግን ዐሥር ሺህ ገዳይ!” እያሉ ዘፈኑ። #1ሳሙ. 21፥11፤ 29፥5። 8ሳኦል ይህ አባባል ደስ ስላላሰኘው በጣም ተቈጥቶ “ለዳዊት ዐሥር ሺህ፥ ለእኔ ግን አንድ ሺህ ብቻ ሰጡ፤ እንግዲህ ከመንገሥ በቀር ምን ቀረው!” አለ። 9ከዚህም የተነሣ ከዚያን ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ ቅናትና ጥርጣሬ አደረበት።
10በማግስቱም በድንገት ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ሳኦልን ተቈራኘው፤ በቤቱም ውስጥ እንደ እብድ ይለፈልፍ ነበር፤ ዳዊትም በየቀኑ ያደርግ በነበረው ዐይነት ለሳኦል በገና ይደረድርለት ነበር፤ ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር። 11“መትቼ ከግድግዳ ጋር አጣብቀዋለሁ!” ብሎ በልቡ አሰበ፤ ከዚህም በኋላ ጦሩን በዳዊት ላይ ሁለት ጊዜ ወረወረ፤ ዳዊት ግን ሁለቴም ዞር እያለ አመለጠ።
12እግዚአብሔር እርሱን ትቶ ከዳዊት ጋር ስለ ነበረ ሳኦል ዳዊትን ፈራው፤ 13ከዚህም የተነሣ ሳኦል ዳዊትን ከፊቱ ለማራቅ የሺህ ወታደሮች አዛዥ አድርጎ ላከው፤ ዳዊትም ወታደሮቹን ወደ ጦርነት መራ። 14እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር። 15ሳኦልም የዳዊትን ተልእኮ መሳካት እየተመለከተ በይበልጥ ይፈራው ጀመር፤ 16ነገር ግን ተልእኮው የሚሳካለት መሪ በመሆኑ በእስራኤልም ሆነ በይሁዳ የሚገኝ ሕዝብ ሁሉ ዳዊትን ይወድ ነበር፤
ዳዊት የሳኦልን ልጅ ማግባቱ
17ከዚህ በኋላ ሳኦል ዳዊትን እንዲህ አለው፥ “የእግዚአብሔርን ጦርነት በጀግንነት ብትዋጋ ታላቅዋን ልጄን ሜራብን እድርልሃለሁ፤” ሳኦል ይህን ያለበት ምክንያት በፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲሞት እንጂ እርሱ ዳዊትን ለመግደል ስላልፈለገ ነው።
18ዳዊትም “የንጉሥ ዐማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ቤተሰቤስ በእስራኤል መካከል እምን ቊጥር ይገባል?” ሲል መለሰለት። 19ነገር ግን ሜራብ ለዳዊት የምትዳርበት ጊዜ ሲደርስ ከመሖላ ለመጣውና ዓድሪኤል ተብሎ ለሚጠራ ለአንድ ሌላ ሰው ተዳረች።
20ይሁን እንጂ ሜልኮል ተብላ የምትጠራው የሳኦል ልጅ ዳዊትን ወደደች፤ ሳኦልም ይህን በሰማ ጊዜ ደስ አለው፤ 21በልቡም “ሜልኮልን ለዳዊት እሰጣለሁ፤ እርስዋም ዳዊትን እንድታጠምድልኝ አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ በፍልስጥኤማውያን እጅ ይገደላል” ሲል አሰበ። ስለዚህም ሳኦል ለሁለተኛ ጊዜ ዳዊትን ጠርቶ “አሁን የእኔ ዐማች ትሆናለህ” አለው። 22ባለሟሎቹንም ጠርቶ “ንጉሡ በአንተ ተደስቶአል፤ የእርሱ ባለሟሎች የሆኑት ባለሥልጣኖቹም ይወዱሃል፤ ስለዚህ የእርሱን ልጅ ታገባ ዘንድ አሁን ጥሩ ጊዜ ገጥሞሃል” ብለው ለዳዊት በግል እንዲነግሩት አዘዘ።
23ስለዚህ የሳኦል ባለሟሎች ይህን ጉዳይ ለዳዊት በምሥጢር ነገሩት፤ እርሱም፦ “እንደእኔ ላለ ዝቅተኛ ድኻ ሰው የንጉሥ ዐማች መሆን ቀላል ይመስላችኋልን?” አላቸው።
24ባለሟሎቹም ከዳዊት ያገኙትን መልስ ለሳኦል ነገሩት፤ 25ሳኦልም እንደ ገና “ንጉሡ ስለ ልጁ ከአንተ የሚፈልገው ጥሎሽ ጠላቶቹን መበቀል እንዲችል አንድ መቶ ፍልስጥኤማውያን ገድለህ ሸለፈታቸውን እንድታመጣለት ብቻ ነው” ብላችሁ ንገሩት ሲል ባለሟሎቹን አዘዘ። ሳኦል ይህን ያደረገበት ምክንያት ዳዊት በፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲገደልለት በማቀድ ነበር። 26የሳኦል ባለሟሎችም ይህንኑ ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም የንጉሡ ዐማች እንዲሆን በመታሰቡ ደስ አለው። የሠርጉም ቀን ከመድረሱ በፊት፥ 27ዳዊትና ወታደሮቹ ዘምተው ሁለት መቶ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ፤ ዳዊትም የንጉሥ ዐማች መሆን ይችል ዘንድ ሸለፈታቸውን ወደ ንጉሡ በመውሰድ ቈጥሮ አስረከበ። ስለዚህም ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ለዳዊት ዳረለት።
28ሳኦል እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር መሆኑንና ልጁም ሜልኮል እርሱን እንደ ወደደችው አረጋገጠ። 29ስለዚህም ሳኦል ዳዊትን ይበልጥ ከመፍራቱ የተነሣ በኖረበት ዘመን ሁሉ የዳዊት ጠላት ሆነ።
30የፍልስጥኤማውያን ወታደሮች በየጊዜው እየመጡ ጦርነት ያደርጉ ነበር፤ ይሁን እንጂ በማናቸውም ጦርነት ሁሉ ከሳኦል የጦር መኰንኖች ይበልጥ ድል የሚሳካለት ለዳዊት ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ዳዊት እጅግ ዝነኛ ሆነ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 18: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997