አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:32-37

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:32-37 አማ05

ዳዊትም ሳኦልን “ንጉሥ ሆይ! ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ ማንም ሰው መፍራት የለበትም! እኔ ያንተ አሽከር ሄጄ እርሱን እዋጋዋለሁ” አለው። ሳኦልም ዳዊትን፦ “አንተ ገና ልጅ ነህ፤ እርሱም ከልጅነቱ ጀምሮ ጦረኛ ስለ ሆነ ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም” አለው። ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ሆይ! እኔ ያንተ አሽከር የአባቴን በጎች የምጠብቅ እረኛ ነኝ፤ አንበሳም ሆነ ድብ መጥቶ ጠቦት በሚነጥቅበት ጊዜ፥ ተከትዬው ሄጄ አደጋ በመጣል የወሰደውን ጠቦት አስጥለው ነበር፤ አንበሳው ወይም ድቡ ወደ እኔ ተመልሶ በሚመጣበትም ጊዜ ጉሮሮውን አንቄ በመምታት እገድለው ነበር። እኔ ያንተ አሽከር አንበሳና ድብ ገድያለሁ፤ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ስለ ተፈታተነ ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ከአንበሳና ድብ ያዳነኝ እግዚአብሔር ከዚህም ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።” ሳኦልም “መልካም ነው! እንግዲህ ሂድ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን!” ሲል መለሰለት።