ዳዊትም በማግስቱ ማልዶ ተነሣ፤ በጎቹን ለሌላ እረኛ በመተው እሴይ ባዘዘው መሠረት የተዘጋጀውን ምግብ ይዞ ሄደ፤ እስራኤላውያን ጦርነት ለመግጠም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሚደነፉበት ጊዜ ዳዊት ወደ ጦሩ ሰፈር ደረሰ። የፍልስጥኤማውያን ሠራዊትና የእስራኤላውያን ሠራዊት ቦታ ቦታቸውን ይዘው በጦሩ ግንባር ፊት ለፊት በመተያየት ላይ ነበሩ። ዳዊትም የያዘውን ምግብ ለስንቅ ጠባቂው ትቶ ወደ ጦሩ ግንባር እየሮጠ ወደ ወንድሞቹ ሄደ፤ ስለ ደኅንነታቸውም ጠየቃቸው። ዳዊትም ከወንድሞቹ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ እነሆ፥ ጎልያድ የተባለው ግዙፍ ፍልስጥኤማዊ የጋት ሰው ከዚያ በፊት ያደርገው እንደ ነበር ወደፊት በማምራት በእስራኤላውያን ላይ መፎከሩን ቀጠለ፤ ዳዊትም የእርሱን ድንፋታ ሰማ። እስራኤላውያንም ጎልያድን ባዩ ጊዜ በታላቅ ፍርሀት ሸሹ። እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸውም እንዲህ ይባባሉ ነበር፤ “ይህ በየቀኑ እስራኤልን ለመፈታተን የሚወጣውን ሰው ታያላችሁን? ንጉሥ ሳኦል እርሱን ለሚገድልለት ሰው ብዙ ሀብት ለመስጠት ቃል ገብቶአል፤ ሴት ልጁንም እንደሚድርለትና የአባቱም ቤተሰብ ከግብር ነጻ እንደሚያደርግለት ተናግሮአል።” ዳዊትም በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች “ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እስራኤልን ከዚህ አሳፋሪ ውርደት ለሚያድን ሰው ምን ይደረግለታል? ኧረ ለመሆኑ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት የሚፈታተን ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም ጎልያድን ለሚገድል ሰው ምን እንደሚደረግለት ነገሩት። የዳዊት ታላቅ ወንድም ኤሊአብም ዳዊት ከሰዎቹ ጋር ሲነጋገር ሰማ፤ እርሱም በዳዊት ላይ በጣም ተቈጥቶ “እዚህ ምን ትሠራለህ? በበረሓ ያሉትንስ እነዚያን ጥቂቶች በጎችህን ለማን ተውካቸው? እኔ ትዕቢተኛነትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ! አሁን የመጣኸው እኮ የጦርነቱን ሁኔታ ለመመልከት ነው!” አለው። ዳዊትም “አሁን እኔ ምን አደረግሁ? ለመጠየቅ እንኳ አልችልምን?” ሲል መለሰለት፤ ከዚያም ወደ ሌላው ሰው መለስ ብሎ ያንኑ ጥያቄ አቀረበለት፤ በጠየቀ ቊጥር የሚያገኘው መልስ ተመሳሳይ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ዳዊት የተናገረውን ቃል ሰምተው ስለ ነበር፥ ሄደው ለሳኦል ነገሩት፤ ሳኦልም ልኮ ዳዊትን አስጠራው። ዳዊትም ሳኦልን “ንጉሥ ሆይ! ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ ማንም ሰው መፍራት የለበትም! እኔ ያንተ አሽከር ሄጄ እርሱን እዋጋዋለሁ” አለው። ሳኦልም ዳዊትን፦ “አንተ ገና ልጅ ነህ፤ እርሱም ከልጅነቱ ጀምሮ ጦረኛ ስለ ሆነ ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም” አለው። ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ሆይ! እኔ ያንተ አሽከር የአባቴን በጎች የምጠብቅ እረኛ ነኝ፤ አንበሳም ሆነ ድብ መጥቶ ጠቦት በሚነጥቅበት ጊዜ፥ ተከትዬው ሄጄ አደጋ በመጣል የወሰደውን ጠቦት አስጥለው ነበር፤ አንበሳው ወይም ድቡ ወደ እኔ ተመልሶ በሚመጣበትም ጊዜ ጉሮሮውን አንቄ በመምታት እገድለው ነበር። እኔ ያንተ አሽከር አንበሳና ድብ ገድያለሁ፤ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ስለ ተፈታተነ ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ከአንበሳና ድብ ያዳነኝ እግዚአብሔር ከዚህም ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።” ሳኦልም “መልካም ነው! እንግዲህ ሂድ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን!” ሲል መለሰለት። ሳኦልም የገዛ ራሱን የጦር ልብስ ለዳዊት አለበሰው፤ ከነሐስ የተሠራውን የራስ ቊር በዳዊት ራስ ላይ ደፍቶ ጥሩርም አለበሰው፤ ዳዊትም ይህን ዐይነት ልብስ ለብሶ ስለማያውቅ ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጥቆ ለመሄድ ሲነሣ መራመድ አልቻለም፤ ስለዚህ ዳዊት ሳኦልን፦ “ያልተለማመድኩት ነገር ስለ ሆነ ይህን ሁሉ ልብስ ለብሼ መዋጋት አልችልም፤” አለ፤ ስለዚህም ያንን ሁሉ አወለቀ፤ በትሩን አንሥቶ፥ ከወንዝ ዳር አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች መርጦ በመልቀም በእረኝነት ኮረጆው ከተተ፤ ወንጭፉንም ይዞ ወደ ፍልስጥኤማዊው ቀረበ። ፍልስጥኤማዊው ጎልያድ ወደ ዳዊት ለመቅረብ መራመድ ጀመረ፤ ጋሻጃግሬውም በፊት በፊቱ ይሄድ ነበር፤ ዳዊት ቀይ፥ መልከ መልካም፥ ትንሽ ልጅ ስለ ነበረ ዳዊትን ጎልያድ ትኲር ብሎ ባየው ጊዜ በንቀት ዐይን ተመለከተው፤ ስለዚህም ጎልያድ ዳዊትን “በትር ይዘህ የምትመጣው እኔ ውሻ ነኝን” ካለው በኋላ በአማልክቱ ስም ረገመው። ቀጥሎም “ወዲህ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞራዎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ “አንተ ሰይፍ፥ ጦርና ሾተል ይዘህ መጥተህብኛል፤ እኔ ደግሞ አንተ በምትፈታተነውና በእስራኤል ሠራዊት አምላክ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ፤ በዚህች ቀን እግዚአብሔር በአንተ ላይ ድልን ያጐናጽፈኛል፤ እኔም ራስህን እቈርጣለሁ፤ የፍልስጥኤማውያንንም ወታደሮች ሥጋ ለአሞራዎችና ለአራዊት ምግብ አድርጌ እሰጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ መላው ዓለም በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡት ሁሉ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍና በጦር አለመሆኑን ያውቃሉ፤ ጦርነቱ የእግዚአብሔር ነውና፤ በእናንተም ላይ ድልን እንድንጐናጸፍ ያደርገናል።” ፍልስጥኤማዊው አደጋ ሊጥልበት ወደ ዳዊት በቀረበ ጊዜ ዳዊት ጎልያድን ለመግጠም ወደ ጦሩ ግንባር እየሮጠ ሄደ። እጁንም ወደ ኮረጆው ከቶ አንዲት ድንጋይ በማውጣት በጎልያድ ላይ ወነጨፈ፤ ድንጋዩም ግንባሩን በጥርቆ ወደ ራስ ቅሉ ገባ፤ ጎልያድም በምድር ላይ በግንባሩ ተደፋ። በዚህም ዐይነት ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ጎልያድን መትቶ በመግደል ድል አደረገ! በእጁም ሰይፍ አልነበረም። ወደ እርሱም ሮጦ በመሄድ በላዩ ላይ ቆመ፤ የጎልያድንም ሰይፍ ከሰገባው በመምዘዝ ራሱን ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም የእነርሱ ዝነኛ ተዋጊ ጎልያድ መገደሉን ባዩ ጊዜ ሸሹ። ከዚህ በኋላ የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እየፎከሩ እነርሱን በመከተል እስከ ጋትና እስከ ዔቅሮን የቅጽር በሮች ድረስ አሳደዱአቸው፤ የፍልስጥኤማውያን ሬሳ እስከ ጋትና እስከ ዔቅሮን ድረስ ወደ ሻዕራይም በሚያደርሰው መንገድ ሁሉ ወደቀ። እስራኤላውያንም እነርሱን አሳደው ከተመለሱ በኋላ ፍልስጥኤማውያን የነበሩበትን ሰፈር ዘረፉ። ዳዊት የጎልያድን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ የጎልያድን የጦር መሣሪያዎች ግን በራሱ ድንኳን አስቀመጠ። ዳዊት ጎልያድን ለመውጋት በሚሄድበት ጊዜ ሳኦል ተመልክቶ የጦሩን አዛዥ አበኔርን “ይህ የማን ልጅ ነው?” ሲል ጠየቀው። አበኔርም “ንጉሥ ሆይ! በሕይወትህ እምላለሁ፤ የማን ልጅ እንደ ሆነ ገና አላወቅሁም” አለው። ሳኦልም “ሄደህ ይህ ወጣት የማን ልጅ እንደ ሆነ አጥንተህ ዕወቅ” ሲል አዘዘው። ስለዚህ ዳዊት ጎልያድን ገድሎ ወደ ጦር ሰፈር በተመለሰ ጊዜ አበኔር ተቀብሎ ወደ ሳኦል አቀረበው፤ በዚህን ጊዜ ዳዊት የጎልያድን ራስ እንደ ያዘ ነበር፤ ሳኦልም “አንተ ወጣት የማን ልጅ ነህ?” ብሎ ጠየቀው። ዳዊትም “የቤተልሔም ነዋሪ የሆነው የአገልጋይህ የእሴይ ልጅ ነኝ” ሲል መለሰለት።
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:20-58
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos