አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 16:1-23

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 16:1-23 አማ05

እግዚአብሔር ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ከንጉሥነት ስለ ሻርኩት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ድረስ ነው? እኔ እርሱ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ ይኖር ዘንድ አልፈልገውም። ይልቅስ የወይራ ዘይት በቀንድ ሞልተህ በመያዝ በቤተልሔም ወደሚኖረው እሴይ ተብሎ ወደሚጠራው ሰው ዘንድ ሂድ፤ እኔ ከእርሱ ልጆች መካከል አንዱን ንጉሥ እንዲሆን መርጬአለሁ።” ሳሙኤልም “ይህን ለማድረግ እንዴት ይቻለኛል? ሳኦል ይህን ቢሰማ ይገድለኛል!” ሲል ጠየቀ። እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ ‘ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ለማቅረብ መጥቻለሁ’ ብለህ ጊደር ይዘህ ሂድ፤ እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ እንዲመጣ ጥራው፤ እኔም የምታደርገውን ነገር እነግርሃለሁ፤ እኔ የምነግርህንም ሰው ቀብተህ ታነግሣለህ።” ሳሙኤልም እግዚአብሔር ያዘዘውን ለማድረግ ወደ ቤተልሔም ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሰ የከተማይቱ መሪዎች በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ ወደ ሳሙኤል ቀርበው “አመጣጥህ ለሰላም ነውን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “አዎ! ለሰላም ነው፤ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀርብ ዘንድ መጥቻለሁ፤ ራሳችሁን በማንጻት ወደ እኔ ኑ” ሲል መለሰላቸው። እሴይና ልጆቹም ራሳቸውን እንዲያነጹ በመንገር ወደ መሥዋዕቱ እንዲመጡ ጠራቸው። እዚያም በደረሱ ጊዜ ሳሙኤል ኤሊአብ ተብሎ የሚጠራውን የእሴይን ልጅ አይቶ “በእግዚአብሔር ፊት የቆመው ይህ ሰው በእርግጥ ለንጉሥነት የተመረጠ ነው” ሲል አሰበ። እግዚአብሔር ግን “የኤሊአብን ቁመት መርዘምና መልከ ቀናነቱን አትይ፤ እኔ እርሱን አልፈለግሁትም፤ እኔ የምፈርደው ሰዎች እንደሚፈርዱት አይደለም፤ ሰው የውጪ መልክን ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው። ከዚህ በኋላ እሴይ አቢናዳብ ተብሎ የሚጠራውን ልጁን ወደ ሳሙኤል አመጣለት፤ ሳሙኤል ግን “እግዚአብሔር ይህኛውንም አልመረጠውም” አለ። ቀጥሎም እሴይ ሻማ ተብሎ የሚጠራውን ልጁን አመጣ፤ ሳሙኤል ግን “እግዚአብሔር ይህኛውንም አልመረጠም” አለ። በዚህም ዐይነት እሴይ ሰባቱንም ልጆቹን አቅርቦ በሳሙኤል ፊት አሰለፋቸው፤ ሳሙኤልም እሴይን “እነሆ፥ ከእነዚህ መካከል እግዚአብሔር አንዱንም አልመረጠም” አለው። “ታዲያ ሌሎች ልጆች የሉህምን?” ሲል ጠየቀው። እሴይም “የሁሉ ታናሽ የሆነ አንድ ልጅ አለ፤ እርሱ ግን ወደ በግ እረኝነት ሄዶአል” ሲል መለሰለት። ሳሙኤልም “እርሱን አስጠርተህ አምጣው፤ እርሱ ሳይመጣ መሥዋዕት አናቀርብም” አለው። ስለዚህም እሴይ ልኮ አስጠራው፤ እርሱ ቀይ፥ መልከ መልካምና ዐይኖቹ የሚያበሩ ጤናማ ወጣት ነበር፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን “የመረጥኩት ሰው ይህ ነውና ተነሥተህ እርሱን ቀባው!” አለው። ሳሙኤልም በወይራ ዘይት የተሞላውን ቀንድ ወስዶ ዳዊትን በወንድሞቹ ፊት ቀባው፤ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት አደረበት፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ ከእርሱ አልተለየም፤ ከዚህም በኋላ ሳሙኤል ወደ ራማ ተመለሰ። የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ስለ ተለየ ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ያሠቃየው ነበር፤ አገልጋዮቹም እንዲህ አሉት፤ “እነሆ ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ያሠቃይሃል፤ ስለዚህ ንጉሥ ሆይ! በገና መደርደር የሚያውቅ ሰው ፈልገን እንድናመጣልህ እዘዘን፤ ከዚያም በኋላ ክፉ መንፈስ በሚመጣብህ ጊዜ ያ ሰው በገና ይደረድርልሃል፤ አንተም እንደገና ጤናማ ትሆናለህ።” ሳኦልም “በገና በመደርደር የታወቀ ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው። ከአገልጋዮቹም አንዱ “የቤተልሔም ከተማ ነዋሪ የሆነው እሴይ በገና መደርደር የሚችል ልጅ እንዳለው አይቼአለሁ ይህም ብቻ ሳይሆን ጀግና፥ መልከ ቀና፥ ብርቱ ወታደርና ንግግር ዐዋቂ ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው” አለው። ስለዚህም ሳኦል ወደ እሴይ መልእክተኞች ልኮ “የበጎች እረኛ የሆነውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” አለው። እሴይም ዳዊትን አንድ ትንሽ የፍየል ጠቦት አስይዞ፥ እንጀራና የወይን ጠጅ የተሞላበት አቁማዳ ከተጫነ አንድ አህያ ጋር ወደ ሳኦል ላከው። ዳዊትም ወደ ሳኦል መጥቶ ሥራውን ጀመረ፤ ሳኦልም በጣም ስለ ወደደው የእርሱ መሣሪያ ያዥ ጋሻጃግሬ አደረገው። ከዚያም በኋላ ሳኦል ወደ እሴይ መልእክት ልኮ “ዳዊትን ወድጄዋለሁ፤ ስለዚህ እዚህ በመቈየት ያገልግለኝ” አለው። ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ ዳዊት በገናውን አንሥቶ ይደረድራል፤ ክፉውም መንፈስ ለቆት ስለሚሄድ ሳኦል እየተሻለው እንደገና ጤናማ ይሆናል።