አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15:17-26

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15:17-26 አማ05

ሳሙኤልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አንተ ስለ ራስህ የነበረህ ግምት አነስተኛ ቢሆንም የእስራኤል ነገዶች መሪ አልሆንክምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቀብቶ አንግሦሃል፤ ኃጢአተኞች የሆኑትን እነዚያን አማሌቃውያንን እንድትደመስስ ልኮሃል፤ እስኪጠፉም ድረስ እነርሱን ግደል ብሎ ነግሮሃል። ታዲያ ስለምን ትእዛዙን አልፈጸምክም? ለምርኮስ በመሳሳትና በመስገብገብ እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኝ ነገር ስለምን አደረግህ?” ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ፤ ባዘዘኝም መሠረት ዘምቻለሁ፤ ንጉሥ አጋግን ብቻ ማርኬ ሳመጣ ሌሎችን ዐማሌቃውያን ሁሉ ገድያለሁ፤ ነገር ግን ወታደሮቼ የማረኩአቸውን ምርጥ ምርጥ የሆኑ በጎችንና የቀንድ ከብቶችን አልገደሉአቸውም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ በጌልገላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ አምጥተዋቸዋል።” ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር የሚወደው የቱን ይመስልሃል? መታዘዝን ወይስ ቊርባንና መሥዋዕት ማቅረብን? ለእርሱ መታዘዝ ምርጥ የበግ መሥዋዕት ከማቅረብ ይበልጣል፤ በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ እንደ ሟርተኛነት፥ የትዕቢት እልኸኛነትም ጣዖትን በማምለክ ኃጢአት እንደ መሥራት ይቈጠራል፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ተውክ በንጉሥነትህ እንዳትቀጥል እርሱም አንተን ትቶሃል።” ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አዎ፤ እኔ ኃጢአት ሠርቼአለሁ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና አንተ የሰጠኸኝን መመሪያ አልጠበቅሁም፤ ወታደሮቼን በመፍራት እነርሱ የፈለጉትን ሁሉ አደረግሁ፤ አሁን ግን እለምንሃለሁ በደሌን ይቅር በለኝ፤ በዚያ ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔም ጋር ወደ ጌልጌላ ተመለሰ።” ሳሙኤልም “እኔ ከአንተ ጋር አልሄድም፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም ትተሃል፤ አንተም የእስራኤል ንጉሥ ሆነህ እንዳትቀጥል እርሱ ትቶሃል” ሲል መለሰለት።