የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12:1-25

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12:1-25 አማ05

ከዚህ በኋላ ሳሙኤል ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ አለ፤ “ጥያቄአችሁን ሁሉ ተቀብዬ ንጉሥ አንግሼላችኋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ የሚመራችሁ ንጉሥ አግኝቼአለሁ፤ እኔ ግን ዕድሜዬ ስለ ገፋ ሸምግዬአለሁ፤ ልጆቼም ከእናንተው ጋር አሉ፤ ከወጣትነት ጊዜዬ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የእናንተ መሪ ሆኜ ቈይቼአለሁ። እነሆ አሁን በፊታችሁ ቆሜአለሁ፤ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ንጉሥ ፊት መስክሩብኝ፤ የማንን በሬ ወስጄአለሁ? የማንንስ አህያ ወስጄአለሁ? ማንንስ አታልዬአለሁ? ማንንስ ጨቊኜአለሁ? ፍርድን ለማዛባት ከማን ላይ ጉቦ ተቀብዬአለሁ? ከእነዚህ ሁሉ አንዱን አድርጌ ከሆነ የወሰድኩትን ለመመለስ ዝግጁ ነኝ።” ሕዝቡም “ከቶ አላታለልከንም፤ አልጨቈንከንም፤ ከማንም ሰው ምንም ነገር አልወሰድክም” ሲሉ መለሱለት። ሳሙኤልም “እንግዲህ ዛሬ በፊታችሁ ንጹሕ ሆኜ ስለ መገኘቴ እግዚአብሔርና እርሱ የመረጠው ንጉሥ ምስክሮች ናቸው” አለ። ሕዝቡም “አዎ! እግዚአብሔር ምስክር ነው!” ሲሉ መለሱለት። ሳሙኤልም የሚናገረውን ቃል በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “ሙሴንና አሮንን የመረጠ፥ የቀድሞ አባቶቻችሁንም ከግብጽ ምድር ያወጣ እግዚአብሔር ነው፤ እንግዲህ ተነሥታችሁ ባላችሁበት ቁሙ፤ የቀድሞ አባቶቻችሁንና እናንተን ለማዳን እግዚአብሔር ያደረገላችሁን ድንቅ ሥራዎች ሁሉ በማስታወስ እነሆ እኔ በእግዚአብሔር ፊት እፋረዳችኋለሁ፤ ያዕቆብና ቤተሰቡ ወደ ግብጽ ወርደው በዚያ ሲኖሩ ግብጻውያን የጭቈና ቀንበር ጫኑባቸው፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም ርዳታ ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን ላከላቸው፤ እነርሱም ከግብጽ መርተው በማውጣት በዚህች ምድር እንዲሰፍሩ አደረጉአቸው፤ ነገር ግን ሕዝቡ አምላካቸውን እግዚአብሔርን ረሱ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሓጾር ሠራዊት አዛዥ ለነበረው ለሲሣራ፥ ለፍልስጥኤማውያን፥ ለሞአብም ንጉሥ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም እስራኤላውያንን ድል ነሡ። ከዚያም በኋላ እነርሱ ‘አንተን ትተን በዓልንና ዐስታሮትን በማምለካችን በድለናል፤ አሁንም ከጠላቶቻችን አድነን፤ እናመልክህማለን!’ ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። እግዚአብሔርም መጀመሪያ ጌዴዎንን፥ ከዚያም በኋላ ባራቅንና ዮፍታሔን፥ ከዚያም ሶምሶንን፥ በመጨረሻም እኔን ላከ፤ እኛም እያንዳንዳችን እናንተን ከጠላቶቻችሁ አዳናችሁ፤ በሰላምም ኖራችሁ፤ እናንተ ግን እግዚአብሔር አምላካችሁ ንጉሣችሁ ሆኖ ሳለ የአሞን ንጉሥ ናዖስ በእናንተ ላይ መነሣቱን ባያችሁ ጊዜ ‘አይሆንም ንጉሥ አንግሥልን’ አላችሁ። “የጠየቃችሁትንና የመረጣችሁትን ንጉሥ እነሆ እግዚአብሔር አነገሠላችሁ፤ እግዚአብሔርን ብትፈሩና ብታመልኩት፥ ቃሉንም ብታዳምጡ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ብትጠብቁ፥ እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ብትከተሉ ሁሉ ነገር ይሠምርላችኋል፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል ባታዳምጡ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ብታምፁ በእናንተና በንጉሣችሁ ላይ የእግዚአብሔር ቅጣት ይበረታባችኋል፤ ስለዚህ ባላችሁበት ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር በፊታችሁ የሚያደርገውንም ድንቅ ነገር ታያላችሁ፤ እነሆ አሁን እንደምታውቁት የፀሐይ ሙቀት የበዛበት የስንዴ መከር ወራት አይደለምን? ነገር ግን እኔ አሁን እጸልያለሁ፤ እግዚአብሔርም ነጐድጓድና ዝናብ ይልካል፤ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ንጉሥ እንዲያነግሥላችሁ በመጠየቃችሁ ምክንያት በደል በመሥራት እግዚአብሔርን ያሳዘናችሁ መሆናችሁን ታረጋግጣላችሁ።” ከዚህም በኋላ ሳሙኤል ጸለየ፤ እግዚአብሔርም በዚያኑ ዕለት ነጐድጓድና ዝናብ ላከ፤ ከዚህም የተነሣ ሕዝቡ እግዚአብሔርንና ሳሙኤልን እጅግ ፈሩ፤ ሳሙኤልንም እንዲህ አሉት፤ “እንዳንሞት እባክህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን፤ ሌላውን ኃጢአት ሁሉ ከመሥራት አልፈን ንጉሥ እንዲያነግሥልን በመጠየቃችን በደለኞች መሆናችንን አሁን ተገንዝበናል።” ሳሙኤልም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “አይዞአችሁ አትፍሩ፤ ይህን የመሰለ ክፉ ነገር ያደረጋችኹ ብትሆኑ እንኳ በሙሉ ልባችሁ እርሱን አገልግሉት እንጂ ፊታችሁን ከእግዚአብሔር ወደ ሌላ አትመልሱ። ዋጋቢስ የሆኑ ጣዖቶችን አታምልኩ፤ እነርሱ ሊረዱአችሁም ሆነ ሊያድኑአችሁ አይችሉም፤ እግዚአብሔር የእርሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ወዶአልና ስለ ታላቅ ስሙ እናንተን ሕዝቡን አይተውም። መልካሙንና ቅኑን ነገር አስተምራችኋለሁ እንጂ ስለ እናንተ መጸለይን በመተው እግዚአብሔርን እበድል ዘንድ ይህ ከእኔ ይራቅ። እግዚአብሔርን ብቻ ፍሩ፤ ያደረገላችሁን ድንቅ ነገሮች ተመልክታችሁ በፍጹም ልባችሁ በታማኝነት አገልግሉት። ኃጢአት በመሥራት ብትጸኑ ግን እናንተም ንጉሣችሁም ትጠፋላችሁ።”