አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 11:1-10

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 11:1-10 አማ05

ሰሎሞን ብዙ የባዕዳን አገሮችን ሴቶች አፈቀረ፤ በዚህም መሠረት ከግብጽ ንጉሥ ልጅ ሌላ የሒታውያን፥ የሞአባውያን፥ የዐሞናውያን፥ የኤዶማውያንና የሲዶናውያን ሴቶች ልጆችን አፈቀረ። እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን፥ “አሕዛብ ሴቶችን ያገባችሁ እንደ ሆነ በእርግጥ ወደ አማልእክታቸው ስለሚስቡአችሁ እነርሱን አታግቡ” ብሎ አስጠንቅቆአቸው ነበር፤ እነዚህን ሰሎሞን የወደዳቸው ሴቶች እግዚአብሔር እንዳይጋቡ ከከለከላቸው ሕዝቦች መካከል ናቸው፤ ሰሎሞን ግን ከእነርሱ ጋር በፍቅር ተሰባበረ። ሰሎሞን የነገሥታት ልጆች የሆኑ ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቊባቶች ነበሩት፤ እነርሱም ሰሎሞንን ከእግዚአብሔር እንዲርቅ አደረጉት፤ በተለይም በዕድሜ እየሸመገለ በሄደ መጠን ለባዕዳን አማልክት እንዲሰግድ አደረጉት፤ ሰሎሞን እግዚአብሔርን በታማኝነት በማገልገል እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሆኖ አልተገኘም። የሲዶናውያን ሴት አምላክ ለነበረችው ለዐስታሮትና ሞሎክ ተብሎ ለሚጠራው ለአጸያፊው ለዐሞናውያን አምላክ ሰገደ። በደል በመሥራትም እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ ሰሎሞን እግዚአብሔርን በቅንነት በመከተል ረገድ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሆኖ አልተገኘም። ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ተራራ ላይ አጸያፊዎች ለሆኑት ከሞሽ ተብሎ ለሚጠራው ለሞአባውያን አምላክና ሞሎክ ተብሎ ለሚጠራው ለዐሞናውያን አምላክ የመስገጃ ስፍራዎችን አዘጋጀላቸው። እንዲሁም የባዕዳን አገሮች ሚስቶቹ ለየአማልክታቸው ዕጣን የሚያጥኑባቸውንና መሥዋዕት የሚያቀርቡባቸውን ስፍራዎች ሠራ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሁለት ጊዜ ተገልጦለት ባዕዳን አማልክትን እንዳያመልክ ያዘዘው ቢሆንም እንኳ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር አልታዘዘም፤ ይልቁንም ከእግዚአብሔር እየራቀ ሄደ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር በሰሎሞን ላይ ተቈጣ፤