አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 1
1
ንጉሥ ዳዊት በሽምግልና ዕድሜው
1ንጉሥ ዳዊት እጅግ ሸምግሎ ስለ ነበር አገልጋዮቹ የብርድ መከላከያ የሚሆን ልብስ ደራርበው ቢያለብሱትም ሙቀት ሊሰጠው አልቻለም ነበር። 2ስለዚህ ባለሟሎቹ “ንጉሥ ሆይ! ከአንተ ጋር ሆና የምትንከባከብህ ወጣት ልጃገረድ ፈልገን እናምጣልህ፤ ከአንተ ጋር ዐቅፋህ በመተኛት ታሞቅሃለች” አሉት። 3አንዲት ቈንጆ ልጃገረድ ለማግኘት በመላው እስራኤል ፍለጋ ተደረገ፤ ሹኔም ተብላ ከምትጠራው ስፍራ አቢሻግ የምትባል አንዲት ልጃገረድ አግኝተው ለንጉሡ አመጡለት፤ 4እርስዋም እጅግ ውብ ነበረች፤ ከንጉሡም ጋር ሆና በማገልገል ትንከባከበው ነበር፤ ይሁን እንጂ እርሱ ከእርስዋ ጋር አልተገናኘም።
አዶንያስ ለመንገሥ የነበረው ፍላጎት
5-6ከአቤሴሎም በኋላ ከዳዊትና ከሐጊት የተወለደ በሕይወት ያለ ተከታይ ልጅ አዶንያስ ነበር፤ እርሱም እጅግ መልከ ቀና ነበር፤ ዳዊት ስለማናቸውም ነገር ምክርና ተግሣጽ ሰጥቶት አያውቅም ነበር፤ ከዚህም የተነሣ አዶንያስ ለመንገሥ ፈለገ፤ ይህንንም ፍላጎቱን ለማሟላት ሠረገሎችን፥ ፈረሶችንና ኀምሳ ጋሻ ጃግሬዎችን አዘጋጀ። #2ሳሙ. 3፥4። 7ስለዚህም ጉዳይ ከጸሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር ተመካከረ፤ እነርሱም ዓላማውን ደገፉ፤ 8ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅ፥ የዮዳሄ ልጅ በናያ፥ ነቢዩ ናታን፥ ሺምዒ፥ ሬዒና የዳዊት የክብር ዘበኞች አዶንያስን አልደገፉም።
9አንድ ቀን አዶንያስ “ዔንሮጌል” ተብሎ በሚጠራው የውሃ ምንጭ አጠገብ የዞሔሌት አለት በሚባለው ስፍራ በጎችን፥ በሬዎችንና የሰቡ ወይፈኖችን ዐርዶ መሥዋዕት አቀረበ፤ የንጉሥ ዳዊትን ልጆችና በይሁዳ የሚገኙትን የመንግሥት ባለሥልጣኖች ሁሉ ወደዚህ ወደ መሥዋዕቱ በዓል መጥተው ተካፋዮች እንዲሆኑ ጋበዛቸው፤ #1፥9 “የዞሔሌት አለት”፦ በዕብራይስጥ የዕባብ አለት ማለት ነው። 10ነገር ግን ነቢዩን ናታንን፥ በናያን፥ የንጉሡን የክብር ዘበኞችና ወንድሙን ሰሎሞንን አልጠራቸውም።
የሰሎሞን መንገሥ
11ከዚህ በኋላ ናታን ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄዶ “ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የሐጊት ልጅ አዶንያስ መንገሡን አልሰማሽምን?” አላት። #2ሳሙ. 12፥24። 12“የራስሽንና የልጅሽን የሰሎሞንን ሕይወት ለማትረፍ እንድትችይ ልምከርሽ። 13ወደ ንጉሥ ዳዊት ገብተሽ ‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ነግሦ በዙፋኔ ይቀመጣል’ ብለህ ለአገልጋይህ በመሐላ ቃል ገብተህልኝ አልነበረምን? ታዲያ፥ አሁን አዶንያስ እንዴት ሊነግሥ ቻለ? ብለሽ ንገሪው”። 14“ከንጉሥ ዳዊት ጋር በምትነጋገሪበት ጊዜ እኔም ወዲያውኑ ገብቼ አንቺ የተናገርሺው ሁሉ እውነት መሆኑን አረጋግጣለሁ” አላት።
15ስለዚህ ቤርሳቤህ ንጉሡን ለማነጋገር ወዳለበት እልፍኝ ገባች፤ ንጉሡ እጅግ ስለ ሸመገለ ሹኔማይቱ ልጃገረድ አቢሻግ በጥንቃቄ ትንከባከበው ነበር፤ 16ቤርሳቤህም ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ ነሣች፤ ንጉሡም “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት።
17ቤርሳቤህም እንዲህ ስትል መለሰች፤ “ጌታዬ ሆይ! ልጄ ሰሎሞን የዙፋንህ ወራሽ ሆኖ እንደሚነግሥና በዙፋንህ እንደሚቀመጥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ስም ምለህ ቃል ገብተህልኝ ነበር፤ 18አሁን ግን ጌታዬ ንጉሡ ሳታውቅ አዶንያስ ነግሦአል። 19ስለዚህ ብዙ ኰርማዎችን፥ የሰቡ ወይፈኖችንና በጎችን መሥዋዕት አቅርቦአል፤ በበዓሉም ላይ እንዲገኙለት የንጉሡን ልጆች ካህኑን አብያታርንና የሠራዊትህን አዛዥ ኢዮአብን ጋብዞአቸዋል፤ አገልጋይህን ሰሎሞንን ግን አልጋበዘውም። 20ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ከአንተ በኋላ የሚነግሠው ማን መሆኑን እንድታስታውቀው በመጠባበቅ ላይ ነው፤ 21ይህን ባታደርግ ግን አንተ ከሞትህ በኋላ ወዲያውኑ ልጄ ሰሎሞንና እኔ እንደ በደለኞች እንቈጠራለን።”
22ቤርሳቤህ ገና ንግግርዋን ሳትጨርስ ነቢዩ ናታን ደረሰ፤ 23የነቢዩም መምጣት ለንጉሡ ተነገረው፤ ናታንም ወደ ውስጥ በመግባት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ፤ 24ናታንም፦ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! አዶንያስ ከአንተ በኋላ ነግሦ በዙፋንህ እንዲቀመጥ አስታውቀሃልን?” አለው። 25አዶንያስ በዛሬው ዕለት ብዙ ጥጆችንና የሰቡ ኰርማዎችን፥ በጎችን ዐርዶ መሥዋዕት አቅርቦአል፤ ሌሎቹን የንጉሡን ልጆች የሠራዊትህን አዛዥ ኢዮአብንና ካህኑን አብያታርን ጋብዞአል፤ እነሆ አሁን በዚህ ሰዓት “ረጅም ዕድሜ ለንጉሥ አዶንያስ!” በማለት እየደነፉ ከእርሱ ጋር በመብላትና በመጠጣት ላይ ናቸው። 26ነገር ግን ይህ ሁሉ ሲሆን እኔን አገልጋይህን፥ ካህኑን ሳዶቅን፥ የዮዳሄን ልጅ በናያንና አገልጋይህን ሰሎሞንን ወደ ግብዣው አልጠራንም፤ 27ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ በዙፋንህ ላይ የሚቀመጠው ማን እንደሚሆን ለባለሟሎችህ ሳታስታውቅ ይህ የአዶንያስ መንገሥ ጉዳይ አንተ ያደረግኸው ነገር ነውን?
28ንጉሥ ዳዊትም “ተመልሳ እንድትመጣ ቤርሳቤህን ጥሩ” ብሎ አዘዘ፤ እርስዋም መጥታ በፊቱ ቆመች፤ 29በዚህም ጊዜ እንዲህ አላት፥ “ከደረሰብኝ መከራ ሁሉ በታደገኝ በሕያው እግዚአብሔር ስም ቃል እገባልሻለሁ፤ 30ልጅሽ ሰሎሞን በእኔ እግር ተተክቶ እንደሚነግሥ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ከዚህ በፊት የገባሁልሽን ቃል በዛሬው ዕለት የምፈጽም መሆኔን አረጋግጥልሻለሁ።”
31ቤርሳቤህም ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ በመንሣት “ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘለዓለም በሕይወት ይኑር!” አለች።
32ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዳዊት ካህኑን ሳዶቅን፥ ነቢዩን ናታንንና የዮዳሄን ልጅ በናያን አስጠራ፤ እነርሱም ገብተው ወደ እርሱ ቀረቡ። 33ንጉሡም እንዲህ አላቸው፦ “በቤተ መንግሥቴ ከሚገኙት ባለሟሎቼ ጋር አብራችሁ ሂዱ፤ ልጄን ሰሎሞንንም እኔ በምቀመጥባት በቅሎ አስቀምጡትና አጅባችሁት ወደ ግዮን ምንጭ ውረዱ፤ 34በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን ቀብተው በእስራኤል ላይ ያንግሡት፤ ከዚህ በኋላ እምቢልታ በመንፋት ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ‘ረጅም ዕድሜ ለንጉሥ ሰሎሞን!’ በሉ። 35በዙፋኔ ላይ ለመቀመጥ ወደዚህ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ አጅባችሁት ኑ፤ የእስራኤልና የይሁዳ ንጉሥ ገዢ እንዲሆን የመረጥኩት ስለ ሆነ እርሱ ከእኔ በኋላ ይነግሣል።”
36የዮዳሄ ልጅ በናያም “ጌታዬ ንጉሡ እንዳለው ይሁን፤ ይህንንም አምላክህ እግዚአብሔር ይፈጽመው። 37ንጉሥ ሆይ! እግዚአብሔር ከአንተ ጋር እንደ ሆነ ሁሉ ከሰሎሞንም ጋር ይሁን፤ መንግሥቱንም በዘመንህ ከነበረው የበለጠ ታላቅ ያድርገው!” አለው።
38ስለዚህ ካህኑ ሳዶቅ፥ ነቢዩ ናታን፥ የዮዳሄ ልጅ በናያና የንጉሡ ክብር ዘበኞች ሰሎሞንን ዳዊት በሚቀመጥባት በቅሎ ላይ በማስቀመጥ ወደ ግዮን ምንጭ ወረዱ፤ 39ካህኑ ሳዶቅም ከተቀደሰው ድንኳን ይዞት የመጣውን የቅባት ዘይት መያዣ ቀንድ ወስዶ ሰሎሞንን ቀባው፤ በዚህን ጊዜ እምቢልታ ነፉ፤ ሕዝቡም ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ረጅም ዕድሜ ለንጉሥ ሰሎሞን!” አሉ፤ 40ወደ ቤተ መንግሥትም በሚመለሱበት ጊዜ አጅበው ተከተሉት፤ ከድምፃቸው ከፍተኛነት የተነሣ ምድር እስክትናወጥ ድረስ እምቢልታ በመንፋት እየጮኹ ደስታቸውን ገለጡ።
41አዶንያስና የጠራቸው ተጋባዦች ሁሉ ግብዣውን በማገባደድ ላይ ሳሉ የሁካታ ድምፅ ሰሙ፤ ኢዮአብም የእምቢልታ ድምፅ በሰማ ጊዜ “ይህ በከተማው ውስጥ የሚሰማው የሁካታ ድምፅ ሁሉ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ፤ 42እርሱ ገና ተናግሮ ሳይጨርስ የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን ድንገት ደረሰ፤ አዶንያስም “እስቲ ና ግባ፤ አንተ ጥሩ ሰው ስለ ሆንክ መልካም ዜና ይዘህ ሳትመጣ አትቀርም” አለው።
43ዮናታንም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ደኅና ወሬስ ይዤ አልመጣሁም፤ ግርማዊው ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አንግሦታል፤ 44ንጉሡም እርሱን ያጅቡት ዘንድ ካህኑን ሳዶቅን፥ ነቢዩን ናታንን፥ የዮዳሄን ልጅ በናያንና የቤተ መንግሥቱን ክብር ዘበኞች ልኮአል፤ እነርሱም ንጉሡ በሚቀመጥባት በቅሎ ላይ እንዲቀመጥ አድርገውታል። 45ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ምንጭ አጠገብ ቀብተው አንግሠውታል፤ ከዚህም በኋላ ሕዝቡ ሁሉ በደስታ ተሞልተው በእልልታና በሆታ ድምፃቸው እያስተጋባ ወደ ከተማ ተመልሰዋል፤ አሁን የምትሰሙትም ድምፅ ይኸው ነው፤ 46እነሆ ሰሎሞን ነግሦ በንጉሣዊ ዙፋን ላይ ተቀምጦአል፤ 47ከዚህም በላይ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ባለሟሎች ሁሉ ወደ ንጉሥ ዳዊት ቀርበው ‘አምላክህ እግዚአብሔር ሰሎሞንን ከአንተ ይበልጥ ዝናው የገነነ፥ መንግሥቱንም ይበልጥ ታላቅ ያድርገው!’ ሲሉ አክብሮታቸውን ገልጠዋል፤ ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዳዊት በአልጋው ላይ ሳለ ለእግዚአብሔር ሰገደ። 48‘ዛሬ ከእኔ ዘሮች መካከል አንዱ በእኔ እግር ተተክቶ እንዲነግሥ ያደረገና ይህን ለማየት ያበቃኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን!’ ሲል እግዚአብሔርን አመሰገነ።”
49አዶንያስ የጠራቸው ተጋባዦች ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ሁሉም ተነሡ፤ እያንዳንዱም በየፊናው ተበተነ፤ 50አዶንያስም ሰሎሞንን ስለ ፈራ ወደ ተቀደሰው ድንኳን ሄዶ የመሠዊያውን ቀንዶች በመያዝ ተማጠነ። 51ሰዎቹም ሰሎሞንን “አዶንያስ አንተን ከመፍራቱ የተነሣ የመሠዊያውን ቀንዶች ይዞ ‘ከሁሉ በፊት ንጉሥ ሰሎሞን የማይገድለኝ መሆኑን በማረጋገጥ በመሐላ ቃል ይግባልኝ’ በማለት እየተማጠነ ነው” ሲሉ ነገሩት።
52ንጉሥ ሰሎሞንም “አካሄዱን ካሳመረ ከራስ ጠጒሩ አንዲት እንኳ አትነካበትም፤ ክፉ ሆኖ ከተገኘ ግን ይሞታል” ሲል መለሰ፤ 53ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን አዶንያስን ከመሠዊያው አውርደው ያመጡት ዘንድ መልእክተኞች ላከ፤ አዶንያስም ወደ ንጉሡ ፊት በመቅረብ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ፤ ንጉሡም “ወደ ቤትህ መሄድ ትችላለህ” አለው።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997