1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8
8
ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋ
1ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋ የሆነ እንደ ሆነ፥ እርግጥ ነው “ሁላችንም ዕውቀት አለን፤” ይሁን እንጂ ዕውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል። 2“ዕውቀት አለኝ” ብሎ የሚያስብ ሰው ቢኖር የሚገባውን ያኽል ገና አላወቀም። 3እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ይሆናል።
4ስለዚህ ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ ስለ መብላት የሆነ እንደ ሆነ ጣዖት ሕይወት የሌለው እንደ ሆነና ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። 5ምንም እንኳ አምላክ ሳይሆኑ አማልክት ተብለው የሚጠሩ ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች በሰማይም ሆነ በምድር አሉ ቢባል 6የእኛ አምላክ ግን የሁሉ ነገር ፈጣሪና እኛም የእርሱ የሆንን አንዱ እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው፤ እንዲሁም ሁሉ ነገር በእርሱ የተፈጠረና እኛም በእርሱ የምንኖር አንዱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።
7ነገር ግን ይህን የሚያውቁ፥ ሁሉም አይደሉም፤ አንዳንዶች እስከ አሁን ድረስ ጣዖትን ማምለክ ስለ ለመዱ ሥጋን የሚበሉት ለጣዖት እንደ ተሠዋ አድርገው ነው፤ ስለዚህ ኅሊናቸው ደካማ በመሆኑ ይረክሳሉ። 8ዳሩ ግን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበን መብል አይደለም፤ ባንበላም የሚጐድልብን ነገር የለም፤ ብንበላም የምናተርፈው ነገር የለም።
9ይሁን እንጂ ይህ ነጻነታችሁ በእምነት ላልጠነከሩ ሰዎች መሰናከያ እንዳይሆንባቸው ተጠንቀቁ። 10“ዕውቀት አለኝ” ብለህ ለጣዖት የተሠዋውን በቤተ ጣዖት ስትበላ በእምነቱ ያልጠነከረ ሰው ቢያይህ ይህ ድርጊትህ ሰውየው ለጣዖት የተሠዋውን እንዲበላ ያደፋፍረው የለምን? 11ስለዚህ በአንተ “ዐዋቂ ነኝ” ባይነት ክርስቶስ የሞተለትና በእምነቱ ያልጠነከረ ክርስቲያን ይጠፋል ማለት ነው። 12በዚሁ ሁኔታ ክርስቲያን ወንድሞቻችሁን በመበደልና ደካማ ኅሊናቸውንም በማቊሰል ክርስቶስን ትበድላላችሁ። 13ስለዚህ ምግብ ክርስቲያን ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከቶ ሥጋ አልበላም።
Currently Selected:
1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997