1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7:1-9

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7:1-9 አማ05

ስለ ጻፋችሁልኝ ጥያቄ ሰው ከሴት ጋር ግንኙነት ባያደርግ መልካም ነው። ነገር ግን ከዝሙት ለመራቅ እያንዳንዱ ወንድ የራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዱዋም ሴት የራስዋ ባል ይኑራት። ባል ለሚስቱ ማድረግ የሚገባውን የጋብቻ መብትዋን አይከልክላት፤ እንዲሁም ሚስት ለባልዋ ማድረግ የሚገባትን የጋብቻ መብቱን አትከልክለው። ሚስት በሰውነቷ ላይ ሥልጣን የላትም፤ በእርስዋ ሰውነት ላይ ሥልጣን ያለው ባልዋ ነው። እንዲሁም ባል በሰውነቱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ በእርሱ ሰውነት ላይ ሥልጣን ያላት ሚስቱ ነች። በጸሎት ለመትጋት ሁለታችሁም ተስማምታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በቀር በመለያየት አንዱ የሌላውን የጋብቻ መብት አይከልክል። በዚህም ምክንያት ራሳችሁን መቈጣጠር አቅቶአችሁ ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ እንደገና አብራችሁ ሁኑ። ይህን ግን የምላችሁ እንደምክር ነው እንጂ እንደ ትእዛዝ አይደለም። ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሚስት ሳያገባ ቢኖር በወደድኩ ነበር፤ ነገር ግን ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር የተለየ ስጦታ ሰጥቶታል፤ አንዱ አንድ ዐይነት ስጦታ፥ ሌላውም ሌላ ዐይነት ስጦታ አለው። ላላገቡና እንዲሁም ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች የምለው እንዲህ ነው፤ ሳያገቡ እንደ እኔ ሆነው ቢኖሩ መልካም ነው። ነገር ግን በሥጋ ምኞት ከመቃጠል ይልቅ ማግባት የተሻለ ነውና ራሳቸውን መቈጣጠር ቢያቅታቸው ያግቡ።