1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5
5
በምእመናን መካከል የተደረገ ምግባረ ብልሹነት
1በመካከላችሁ አሳፋሪ የዝሙት ሥራ መኖሩ ይወራል፤ እንዲህ ዐይነቱ የዝሙት ሥራ በአሕዛብ ዘንድ እንኳ የማይደረግ ነው፤ ይኸውም የእንጀራ እናቱን እንደ ሚስት አድርጎ የሚኖር አለ ተብሎአል። #ዘዳ. 22፥30። 2ታዲያ፥ እንዲህ ያለ አሳፋሪ ነገር በመካከላችሁ እያለ ለምን ትታበያላችሁ? ይልቅስ በዚህ ነገር ማዘን አይገባችሁምን? እንዲህ ዐይነቱን ሥራ የፈጸመውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱ። 3ምንም እንኳ እኔ በሥጋ አብሬአችሁ ባልሆን በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ልክ አብሬአችሁ እንዳለሁ ሆኜ እንዲህ ዐይነቱን ሥራ በፈጸመው ሰው ላይ በጌታ በኢየሱስ ስም ፈርጄበታለሁ፤ 4በምትሰበሰቡበት ጊዜ እኔም በጌታችን በኢየሱስ ኀይል በመካከላችሁ በመንፈስ ስለምገኝ፥ 5በኃጢአት የተሞላው የዚህ ሰው ሥጋ ይፈርስ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፋችሁ ልትሰጡት ይገባል። ይህንንም የምታደርጉት ጌታ ኢየሱስ ለፍርድ በሚመጣበት ቀን የዚህ ሰው ነፍስ እንድትድን ነው።
6እንግዲህ መመካታችሁ መልካም አይደለም፤ ትንሽ እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው ታውቁ የለምን? #ገላ. 5፥9። 7አሁን እንደ ሆናችሁት ሁሉ እርሾ እንደሌለበት እንደ አዲስ ሊጥ እንድትሆኑ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ የፋሲካችን በግ የሆነው ክርስቶስ ተሠውቶአል፤ #ዘፀ. 12፥5። 8ስለዚህ ተንኰልና ክፋት በሞላበት በአሮጌ እርሾ ሳይሆን እርሾ በሌለበት የቅንነትና የእውነት ቂጣ በዓላችንን እናክብር። #ዘፀ. 13፥3፤ ዘዳ. 16፥3።
9ከዚህ በፊት በጻፍኩላችሁ መልእክት ከአመንዝራዎች ጋር አትተባበሩ ብያችሁ ነበር። 10ይህንንም ስል በአጠቃላይ ከዚህ ዓለም አመንዝራዎች ወይም ከስግብግብ ግለሰቦች ወይም ከሌቦች ወይም ከጣዖት አምላኪዎች ጋር አትተባበሩ ማለቴ አይደለም፤ እንዲህማ ከሆነ ከዓለም መውጣት ያስፈልጋችሁ ነበር ማለት ነው። 11እኔ ግን የጻፍኩላችሁ ክርስቲያኖች ተብለው ከሚያመነዝሩ፥ ወይም ከሚስገበገቡ፥ ወይም ጣዖት ከሚያመልኩ፥ ወይም የሰውን ስም ከሚያጠፉ፥ ወይም ከሚሰክሩ፥ ወይም ከቀማኞች ጋር አትተባበሩ ብዬ ነው። እንደእነዚህ ካሉት ሰዎች ጋር፥ መብል አብራችሁ አትብሉ።
12ከክርስቲያናዊ ማኅበር ውጪ ባሉት ሰዎች ላይ ለመፍረድ እኔ ማን ነኝ? በክርስቲያናዊ ማኅበር ውስጥ ስላሉት ሰዎች ጉዳይ እናንተስ መፍረድ ትችሉ የለምን? 13በውጪ ስላሉት ሰዎች ጉዳይ የሚፈርድ እግዚአብሔር ነው፤ እንግዲህ መጽሐፍ እንደሚል “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱ።”
Currently Selected:
1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997