1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12:3-11

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12:3-11 አማ05

ስለዚህ በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርቶ ኢየሱስን የሚረግም ማንም የለም፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ካልሆነ በቀር “ኢየሱስ ጌታ ነው!” የሚል ማንም እንደሌለ እነግራችኋለሁ። ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አሉ፤ መንፈስ ቅዱስ ግን አንድ ነው። ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፤ ጌታ ግን አንድ ነው። ልዩ ልዩ የሥራ ዐይነቶችም አሉ፤ ነገር ግን ሁሉንም በሁሉ የሚያከናውን አንዱ እግዚአብሔር ነው። ለእያንዳንዱ መንፈስ ቅዱስን የመግለጥ ስጦታ የሚሰጠው ለጋራ ጥቅም ነው። መንፈስ ቅዱስ ለአንዱ ሰው በጥበብ የመናገር ችሎታን ይሰጠዋል፤ ለሌላው ሰው ደግሞ ያው መንፈስ በዕውቀት የመናገርን ችሎታ ይሰጠዋል፤ ያው አንዱ መንፈስ ለአንዱ እምነትን ይሰጠዋል፤ ለሌላውም የመፈወስ ስጦታን ይሰጠዋል፤ እንዲሁም ለአንዱ ተአምራትን የማድረግ ኀይል ይሰጠዋል፤ ለሌላው የትንቢትን ቃል የመናገር ችሎታ ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ ስጦታዎች ከመንፈስ ቅዱስ መሆናቸውን ወይም ከርኩሳን መናፍስት መሆናቸውን ለይቶ የማወቅ ችሎታን ይሰጠዋል፤ እንዲሁም ለአንዱ በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ችሎታን ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ በተለያዩ ቋንቋዎች የተነገረውን የመተርጐም ችሎታን ይሰጠዋል፤ ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ እንደ ፈቀደ ለእያንዳንዱ ሰው የተለየ ስጦታን ይሰጠዋል።