የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12:12-26

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12:12-26 አማ05

አንድ ሰው ብዙ የአካል ክፍሎች አሉት፤ የአካል ክፍሎች ብዙዎች ሆነው ሳሉ የሚገኙት በዚያው በአንዱ አካል ነው። እንዲሁም ክርስቶስ ብዙ የሰውነት ክፍሎች እንዳሉት እንደ አንድ አካል ነው። አይሁድም ብንሆን የግሪክ ሰዎች ብንሆን፤ ባሪያዎችም ብንሆን፥ ነጻ ሰዎችም ብንሆን፥ አንድ ሰውነት ለመሆን በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀናል፤ ሁላችንም ከዚሁ ከአንዱ መንፈስ ጠጥተናል። አንድ አካል የተሠራው ከብዙ የአካል ክፍሎች እንጂ ከአንድ የአካል ክፍል ብቻ አይደለም! እግር “እኔ እጅ ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም!” ቢል ታዲያ እንዲህ በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? ጆሮም “እኔ ዐይን ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል፥ ታዲያ፥ እንዲህ በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? አንድ አካል በሙሉ ዐይን ብቻ ቢሆን ኖሮ በምን መስማት ይቻል ነበር? አንድ አካል በሙሉ ጆሮ ብቻ ቢሆን ኖሮ በምን ማሽተት ይቻል ነበር? አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ፈለገው እያንዳንዱን የአካል ክፍል በአካል ውስጥ ተገቢ ስፍራውን ይዞ እንዲገኝ አድርጎታል። ሁላቸውም አንድ ክፍል ብቻ ቢሆን ኖሮ ሙሉ አካል የት በተገኘ ነበር! አሁን ግን ብዙ የአካል ክፍሎች ቢኖሩም አካል ግን አንድ ብቻ ነው። ዐይን እጅን “አንተ አታስፈልገኝም!” ሊለው አይችልም፤ ራስም እግርን “አንተ አታስፈልገኝም!” ሊለው አይችልም፤ እንዲያውም በጣም ደካሞች መስለው የሚታዩ የአካል ክፍሎች ይበልጥ አስፈላጊ ናቸው። አነስተኛ ክብር ያላቸው መስለው ለሚታዩን የአካል ክፍሎች ይበልጥ ክብር እንሰጣቸዋለን፤ ለማየት የሚያሳፍሩ መስለው ለሚታዩን የሰውነት ክፍሎች ይበልጥ ክብር ሰጥተን እንጠነቀቅላቸዋለን፤ ፊት ለፊት ለሚታዩት የአካል ክፍሎች ግን ይህ ሁሉ አያስፈልጋቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ለማየት የሚያሳፍሩ መስለው የሚታዩንን የአካል ክፍሎች በበለጠ ክብር እንዲያዙ አድርጎ የአካል ክፍሎችን አገጣጥሞአል። ይህንንም ያደረገው በአካል ክፍሎች መካከል መለያየት ሳይኖር እርስ በርሳቸው እንዲተሳሰቡ ነው። አንዱ የአካል ክፍል ሲሠቃይ ሌሎችም የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረው ይሠቃያሉ፤ አንዱ የሰውነት ክፍል ሲከበር ሌሎቹም የሰውነት ክፍሎች አብረው ከእርሱ ጋር ይደሰታሉ።