የመስቀሉ ነገር ለሚጠፉት ሰዎች እንደ ሞኝነት ይቈጠራል፤ ለምንድን ለእኛ ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው። “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የሊቃውንትንም ዕውቀት አስወግዳለሁ” ተብሎ ተጽፎአል። ታዲያ፥ ጥበበኛ የት አለ? የሕግ ምሁርስ የት አለ? ተመራማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ጥበብ ሞኝነት አድርጎት የለምን? የዚህ ዓለም ሰዎች በገዛ ጥበባቸው እግዚአብሔርን ማወቅ እንዳይችሉ እግዚአብሔር በጥበቡ ዘጋባቸው፤ ነገር ግን እንደ ሞኝነት በሚቈጠረው እኛ በምናስተምረው ወንጌል የሚያምኑትን ለማዳን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖአል። መቼም አይሁድ ተአምር ማየትን ይፈልጋሉ፤ የግሪክ ሰዎች ደግሞ ጥበብን ይሻሉ። እኛ ግን ክርስቶስ ስለ እኛ መሰቀሉን እናስተምራለን፤ ይህም ለአይሁድ መሰናከያ ነው፤ ለግሪክ ሰዎች ደግሞ ሞኝነት ነው። ለተጠሩት ግን ለአይሁድም ሆነ ለግሪክ ሰዎች፥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይልና የእግዚአብሔር ጥበብ ነው። የእግዚአብሔር ሞኝነት ነው ተብሎ የሚታሰበው ነገር ከሰው ጥበብ ይበልጣል፤ የእግዚአብሔር ደካማነት ነው ተብሎ የሚታሰበውም ነገር ከሰው ኀይል ይበልጣል። ወንድሞቼ ሆይ! እግዚአብሔር በጠራችሁ ጊዜ ምን ዐይነት ሰዎች እንደ ነበራችሁ አስታውሱ፤ እንደ ሰው አስተሳሰብ ከእናንተ መካከል ብዙዎች ጥበበኞች ወይም ብርቱዎች ወይም ታላላቅ ሰዎች አልነበሩም። እግዚአብሔር ጥበበኞችን ለማሳፈር በዓለም እንደ ሞኞች የሚቈጠሩትን ሰዎች መረጠ፤ ብርቱዎችንም ለማሳፈር በዓለም እንደ ደካሞች የሚቈጠሩትን መረጠ፤ እግዚአብሔር በዓለም ሰዎች ዘንድ አሉ ተብለው የሚታዩትን ነገሮች እንደሌሉ ለማድረግ በዓለም የተዋረደና የተናቀ ከንቱም መስሎ የሚታየውን ነገር መረጠ። ይህንንም ያደረገው ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ ነው። እናንተን ግን እግዚአብሔር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ አደረገ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ጥበባችን፥ ጽድቃችን፥ ቅድስናችንና ቤዛችን እንዲሆን አደረገው። እንግዲህ በመጽሐፍ እንደ ተጻፈው “የሚመካ በጌታ ይመካ።”
1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1:18-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች