አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 24

24
ለካህናት የተሰጠ የሥራ ኀላፊነት
1የአሮን ልጆች የሚከተሉት ናቸው፦ አሮን አራት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ናዳብ፥ አቢሁ፥ አልዓዛርና ኢታማር ተብለው የሚጠሩ ናቸው፤ 2ናዳብና አቢሁ ምንም ዘር ሳይተኩ አባታቸው ከመሞቱ በፊት ሞቱ፤ ስለዚህ የእነርሱ ወንድሞች አልዓዛርና ኢታማር ካህናት ሆኑ፤ 3ንጉሥ ዳዊት የአሮንን ዘሮች እንደየሥራ ምድባቸው በቡድን በቡድን ከፈላቸው፤ ይህንንም ያደረገው የአልዓዛር ዘር በሆነው በሳዶቅና የኢታማር ዘር በሆነው በአቤሜሌክ ረዳትነት ነው። 4የአልዓዛር ቤተሰብ ቊጥር ከኢታማር ቤተሰብ ቊጥር በልጦ ስለ ተገኘ አመዳደቡም በዚሁ መሠረት ተወሰነ፤ ስለዚህ የአልዓዛር የቤተሰብ አለቆች ቊጥር ዐሥራ ስድስት ሆኖ ሲደለደል የኢታማር አለቆች ቊጥር ስምንት እንዲሆን ወሰነ። 5በአልዓዛርና በኢታማር ዘሮች መካከል የቤተ መቅደስ ባለሥልጣኖችና መንፈሳውያን መሪዎች ይገኙ ስለ ነበር፥ የሥራ መደብ ክፍፍል የሚደረገው በዕጣ ነበር። 6ዕጣውንም በቅድሚያ ለማውጣት የአልዓዛርና የኢታማር ዘሮች ተራ ይገቡ ነበር፤ ከዚህም በኋላ በሌዋዊው ጸሐፊ በናትናኤል ልጅ በሸማዕያ ይመዘግቡ ነበር፤ ንጉሡና ባለሟሎቹ የሆኑት ባለሥልጣኖች፥ ካህናቱ ሳዶቅና የአብያታር ልጅ አቤሜሌክ፥ እንዲሁም የካህናትና የሌዋውያን ቤተሰቦች አለቆች ሁሉ ምስክሮች ነበሩ።
7-18ኻያ አራቱ የቤተሰብ ቡድኖች በዕጣ የወጣላቸው የሥራ ምድቡ ክፍፍል ቅደም ተከተል ተራ እንደሚከተለው ነው፦
አንደኛ በይሆያሪብ የሚመራው ቡድን፥
ሁለተኛ በይዳዕያ የሚመራው ቡድን፥
ሦስተኛ በሐሪም የሚመራው ቡድን፥
አራተኛ በሰዖሪም የሚመራው ቡድን፥
አምስተኛ በማልኪያ የሚመራው ቡድን፥
ስድስተኛ በሚያሚን የሚመራው ቡድን፥
ሰባተኛ በሀቆጽ የሚመራው ቡድን፥
ስምንተኛ በአቢያ የሚመራው ቡድን፥
ዘጠነኛ በኢያሱ የሚመራው ቡድን፥
ዐሥረኛ በሸካንያ የሚመራው ቡድን፥
ዐሥራ አንደኛ በኤልያሺብ የሚመራው ቡድን፥
ዐሥራ ሁለተኛ በያቂም የሚመራው ቡድን፥
ዐሥራ ሦስተኛ በሑፓ የሚመራው ቡድን፥
ዐሥራ አራተኛ በዬሼብአብ የሚመራው ቡድን፥
ዐሥራ አምስተኛ በቢልጋ የሚመራው ቡድን፥
ዐሥራ ስድስተኛ በኢሜር የሚመራው ቡድን፥
ዐሥራ ሰባተኛ በሔዚር የሚመራው ቡድን፥
ዐሥራ ስምንተኛ በሃፒጼጽ የሚመራው ቡድን፥
ዐሥራ ዘጠነኛ በፐታሕያ የሚመራው ቡድን፥
ኻያኛ በይሔዝቄል የሚመራው ቡድን፥
ኻያ አንደኛ በያኪን የሚመራው ቡድን፥
ኻያ ሁለተኛ በጋሙል የሚመራው ቡድን፥
ኻያ ሦስተኛ በደላያ የሚመራው ቡድን፥
ኻያ አራተኛ በማዓዝያ የሚመራው ቡድን።
19እነዚህም ሰዎች የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የቀድሞ አባታቸውን አሮንን ባዘዘው መሠረት ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው የሥራ ድርሻቸው ክፍፍል ይህ ነው።
የሌዋውያን ስም ዝርዝር
20የሌዊ ልጆች የቤተሰብ አለቆች የሆኑ ስማቸው ከዚህ በታች የተመለከተው ነው፦
ዬሕደያ በሸቡኤል በኩል የዓምራም ዘር ነው፤ 21ዩሺያ የረሐብያ ዘር ነው፤ 22ያሐት በሸሎሚት በኩል የይጽሃር ዘር ነው፤ 23ይሪያ፥ አማርያ፥ ያሕዚኤልና ይቃምዓም የኬብሮን ልጆች ናቸው፤ እነርሱም ስማቸው የተመዘገበው በዕድሜአቸው ቅደም ተከተል ነው።
24ሻሚር በሚካ በኩል የዑዚኤል ዘር ነው፤ 25ዘካርያስ በሚካ ወንድም በዩሺያ በኩል የዑዚኤል ዘር ነው፤ 26ማሕሊ፥ ሙሺና ያዕዚያ የመራሪ ዘሮች ናቸው፤ 27ያዕዚያም ሾሃም፥ ዛኩርና ዒብሪ ተብለው የሚጠሩ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት። 28-29ማሕሊም አልዓዛርና ቂሽ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ አልዓዛር አንድም ወንድ ልጅ አልነበረውም፤ ቂሽ ግን ይራሕመኤል ተብሎ የሚጠራ አንድ ወንድ ልጅ ነበረው። 30የሙሺም ልጆች፥ ማሕሊ፥ ዔዴርና ያሪሞት ነበሩ።
እንግዲህ እነዚህ ሁሉ የሌዊ ዘር ቤተሰቦች ናቸው።
31የእያንዳንዱ ቤተሰብ አለቃና ታናሹ እንደ ታላቁ በእኩልነት ልክ ዘመዶቻቸው የአሮን ልጆች የነበሩት ካህናት ያደርጉት በነበረው ዐይነት ለሥራቸው ምድብ ዕጣ ይጥሉ ነበር፤ ንጉሥ ዳዊት፥ ሳዶቅ፥ አቤሜሌክና የካህናትና የሌዋውያን ቤተሰቦች አለቆች ሁሉ በተገኙበት ዕጣ ተጣጥለዋል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ