የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16:7-36

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16:7-36 አማ05

ዳዊት፥ ለአሳፍና ለቀሩት ሌዋውያን ወገኖቹ ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር የማቅረብ ኀላፊነት የሰጣቸው በዚያን ጊዜ ነበር። እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ያደረገውንም ሁሉ ለሕዝቦች ንገሩ፤ ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር ዘምሩ፤ ያደረገውን አስደናቂ ነገር ሁሉ ተናገሩ፤ በቅዱስ ስሙ ደስ ይበላችሁ! እግዚአብሔርን የሚፈልግ ሰው ሁሉ ሐሴት ያድርግ! በእግዚአብሔርና በኀያል ሥልጣኑ ተማመኑ፤ ዘወትርም እርሱን ፈልጉ፤ አገልጋዮቹ የሆናችሁ የእስራኤል ልጆች ሆይ! የእግዚአብሔር ምርጥ የሆናችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ! እግዚአብሔር ያደረጋቸውን ድንቅ ነገሮች፥ የሰጠውን ፍርድና ያደረጋቸውን ተአምራት አስታውሱ። እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱም በዓለም ሁሉ ነው። ቃል ኪዳኑን ወይም የሰጠውን ተስፋ እስከ ሺህ ትውልድም ሆነ ለዘለዓለም አይረሳም። ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ይጠብቃል፤ ለይስሐቅ የሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸናል፤ ለያዕቆብም ሥርዓት ለእስራኤል ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን አድርጎ አጸና። ይህም ቃል ኪዳን፥ “የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ፤ ለአንተም የተመደበ ርስትም ይሆናል” የሚል ነው። ይህም የሆነው፥ እነርሱ በቊጥር አነስተኞች ለሀገሩም እንግዶች ሆነው ሳለ ነው። ከአንድ ሕዝብ ወደ ሌላ ሕዝብ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ተንከራተቱ፤ እግዚአብሔር ግን ማንም እንዲጨቊናቸው አልፈቀደም፤ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ። “የተመረጡ አገልጋዮቼን አትንኩ። ነቢያቴንም አትጒዱ” በማለት አስጠነቀቃቸው። በምድር የምትኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ለእግዚአብሔር ዘምሩ! የአዳኝነቱን መልካም ዜና በየቀኑ አብሥሩ፤ በሕዝቦች መካከል ክብሩን አስታውቁ፤ ለሕዝቦችም ሁሉ ታላቅ ሥራውን አውሩ። እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ ከፍ ያለ ምስጋናም ይገባዋል፤ ከአማልክት ሁሉ ይበልጥ ሊፈራ ይገባዋል፤ ሌሎች ሕዝቦች የሚሰግዱላቸው አማልክት ጣዖቶች ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን የፈጠረ አምላክ ነው። በዙሪያው ያለው ክብርና ግርማ ነው፤ መቅደሱንም ኀይልና ደስታ እንዲሞላበት አድርጎአል። በምድር የምትኖሩ ሕዝቦች ሁሉ! ስለ ክብሩና ስለ ኀይሉ እግዚአብሔርን አመስግኑት። ለስሙ ተገቢ የሆነውን ክብር ለእግዚአብሔር ስጡ፤ ወደ መቅደሱም መባ ይዛችሁ ቅረቡ፤ ግርማ በተመላ ቅድስናው ለእግዚአብሔር ስገዱ። የምድር ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ተንቀጥቀጡ! ምድር በጽኑ ስለ ተመሠረተች አትናወጥም። ሰማይና ምድር ደስ ይበላቸው! ሕዝቦች ሁሉ “እግዚአብሔር ንጉሥ ነው” ይበሉ። ባሕርና በውስጡ ያሉት ሁሉ እልል ይበሉ! ማሳና በላይዋ የሚገኙ ሰብሎች ሁሉ ደስ ይበላቸው! እግዚአብሔር በምድር ላይ ሊፈርድ ስለሚመጣ በደን ውስጥ ያሉ ዛፎች በፊቱ እልል ይበሉ! ቸር ስለ ሆነ፥ ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ! እግዚአብሔርንም፥ “አዳኝ አምላካችን ሆይ! ከአሕዛብ መካከል መልሰህ ወደ አገራችን አግባን፤ በዚያን ጊዜ እናመሰግን ዘንድ፥ ቅዱስ ስምህንም እናከብር ዘንድ፥ እባክህ ታደገን!” በሉት። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን! ሕዝቡ ሁሉ “አሜን” አሉ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ።