አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16
16
1የቃል ኪዳኑንም ታቦት ወስደው ዳዊት ባዘጋጀው ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ ከዚያም በኋላ በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንና የኅብረት መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር አቀረቡ፤ 2ዳዊት መሥዋዕት የማቅረቡን ሥነ ሥርዓት ከጨረሰ በኋላ ሕዝቡን በእግዚአብሔር ስም ባረከ፤ 3ለእስራኤላውያን ምግብ አከፋፈለ፤ ለወንድም ሆነ ለሴት በእስራኤል ለሚኖር እያንዳንዱ ሰው አንድ ሙልሙል ዳቦ፥ አንድ ቊራጭ ሥጋና ጥቂት ዘቢብ ሰጠ።
4በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ሆነው ምስጋና፥ ውዳሴና ክብር በማቅረብ ለእግዚአብሔር አምላክ የሚደረገውን የአምልኮ ሥነ ሥርዓት እንዲመሩ ዳዊት ጥቂት ሌዋውያንን ሾመ። 5አሳፍ መሪ፥ ዘካርያስም የእርሱ ረዳት ሆነው ተሾሙ፤ ይዒኤል፥ ሸሚራሞት፥ ይሒኤል፥ ማቲትያ፥ ኤሊአብ፥ በናያ፥ ዖቤድኤዶምና ይዒኤል መሰንቆና በገና ለመደርደር፥ አሳፍም ጸናጽል ለማንሿሿት ተመደቡ፤ 6በናያና ያሐዚኤል ተብለው የሚጠሩት ሁለት ካህናት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ዘወትር እምቢልታ እንዲነፉ ተመደቡ፤ 7ዳዊት፥ ለአሳፍና ለቀሩት ሌዋውያን ወገኖቹ ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር የማቅረብ ኀላፊነት የሰጣቸው በዚያን ጊዜ ነበር።
የምስጋና መዝሙር
(መዝ. 105፥1-15፤ 96፥1-13፤ 106፥1፤47-48)
8እግዚአብሔርን አመስግኑ፤
ስሙንም ጥሩ፤
ያደረገውንም ሁሉ ለሕዝቦች ንገሩ፤
9ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር ዘምሩ፤
ያደረገውን አስደናቂ ነገር ሁሉ ተናገሩ፤
10በቅዱስ ስሙ ደስ ይበላችሁ!
እግዚአብሔርን የሚፈልግ ሰው ሁሉ ሐሴት ያድርግ!
11በእግዚአብሔርና በኀያል ሥልጣኑ ተማመኑ፤
ዘወትርም እርሱን ፈልጉ፤
12-13አገልጋዮቹ የሆናችሁ የእስራኤል ልጆች ሆይ!
የእግዚአብሔር ምርጥ የሆናችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ!
እግዚአብሔር ያደረጋቸውን ድንቅ ነገሮች፥ የሰጠውን ፍርድና
ያደረጋቸውን ተአምራት አስታውሱ።
14እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤
ፍርዱም በዓለም ሁሉ ነው።
15ቃል ኪዳኑን ወይም የሰጠውን ተስፋ እስከ ሺህ ትውልድም ሆነ
ለዘለዓለም አይረሳም።
16ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ይጠብቃል፤
ለይስሐቅ የሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸናል፤ #ዘፍ. 12፥7፤ 26፥3።
17ለያዕቆብም ሥርዓት
ለእስራኤል ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን
አድርጎ አጸና።
18ይህም ቃል ኪዳን፥
“የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ፤
ለአንተም የተመደበ ርስትም ይሆናል” የሚል ነው። #ዘፍ. 18፥13።
19ይህም የሆነው፥ እነርሱ በቊጥር አነስተኞች
ለሀገሩም እንግዶች ሆነው ሳለ ነው።
20ከአንድ ሕዝብ ወደ ሌላ ሕዝብ
ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ተንከራተቱ፤
21እግዚአብሔር ግን ማንም እንዲጨቊናቸው አልፈቀደም፤
ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ።
22“የተመረጡ አገልጋዮቼን አትንኩ።
ነቢያቴንም አትጒዱ” በማለት አስጠነቀቃቸው። #ዘፍ. 20፥3-7።
23በምድር የምትኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ለእግዚአብሔር ዘምሩ!
የአዳኝነቱን መልካም ዜና በየቀኑ አብሥሩ፤
24በሕዝቦች መካከል ክብሩን አስታውቁ፤
ለሕዝቦችም ሁሉ ታላቅ ሥራውን አውሩ።
25እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤
ከፍ ያለ ምስጋናም ይገባዋል፤
ከአማልክት ሁሉ ይበልጥ ሊፈራ ይገባዋል፤
26ሌሎች ሕዝቦች የሚሰግዱላቸው አማልክት ጣዖቶች ናቸው፤
እግዚአብሔር ግን ሰማያትን የፈጠረ አምላክ ነው።
27በዙሪያው ያለው ክብርና ግርማ ነው፤
መቅደሱንም ኀይልና ደስታ እንዲሞላበት አድርጎአል።
28በምድር የምትኖሩ ሕዝቦች ሁሉ!
ስለ ክብሩና ስለ ኀይሉ እግዚአብሔርን አመስግኑት።
29ለስሙ ተገቢ የሆነውን ክብር ለእግዚአብሔር ስጡ፤
ወደ መቅደሱም መባ ይዛችሁ ቅረቡ፤
ግርማ በተመላ ቅድስናው ለእግዚአብሔር ስገዱ።
30የምድር ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ተንቀጥቀጡ!
ምድር በጽኑ ስለ ተመሠረተች አትናወጥም።
31ሰማይና ምድር ደስ ይበላቸው!
ሕዝቦች ሁሉ “እግዚአብሔር ንጉሥ ነው” ይበሉ።
32ባሕርና በውስጡ ያሉት ሁሉ እልል ይበሉ!
ማሳና በላይዋ የሚገኙ ሰብሎች ሁሉ ደስ ይበላቸው!
33እግዚአብሔር በምድር ላይ ሊፈርድ ስለሚመጣ
በደን ውስጥ ያሉ ዛፎች በፊቱ እልል ይበሉ!
34ቸር ስለ ሆነ፥ ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ፥
እግዚአብሔርን አመስግኑ! #2ዜ.መ. 5፥13፤ 7፥3፤ ዕዝ. 3፥11፤ መዝ. 100፥5፤ 106፥1፤ 107፥1፤ 118፥1፤ 136፥1፤ ኤር. 33፥11።
35እግዚአብሔርንም፥
“አዳኝ አምላካችን ሆይ!
ከአሕዛብ መካከል መልሰህ ወደ አገራችን አግባን፤
በዚያን ጊዜ እናመሰግን ዘንድ፥
ቅዱስ ስምህንም እናከብር ዘንድ፥
እባክህ ታደገን!” በሉት።
36የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር
ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም
የተመሰገነ ይሁን!
ሕዝቡ ሁሉ “አሜን” አሉ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ።
በኢየሩሳሌምና በገባዖን የተደረገ የአምልኮ ሥነ ሥርዓት
37ንጉሥ ዳዊት አሳፍንና ሌዋውያን የሆኑትን ወገኖቹን የቃል ኪዳኑ ታቦት ባለበት ስፍራ ለሚካሄደው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ለዘለቄታው ኀላፊዎች እንዲሆኑ አደረጋቸው፤ በዚያም አገልግሎታቸውን በየቀኑ ይፈጽሙ ነበር፤ 38እነርሱንም እንዲረዱ የይዱቱን ልጅ ዖቤድኤዶምና ከእርሱ ጐሣ ሌሎች ሥልሳ ስምንት ሰዎች ተመደቡ፤ የይዱቱን ልጅ ዖቤድኤዶምና ሖሳ ለቅጽር በሮቹ ጥበቃ ኀላፊዎች ሆኑ።
39ካህኑን ሳዶቅንና የእርሱ ወገኖች የሆኑትን ሌሎቹን ካህናት በገባዖን ባለው እግዚአብሔር በሚመለክበት ድንኳን ለሚደረገው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ኀላፊዎች እንዲሆኑ አደረጋቸው። 40ይህንንም ያደረገው እግዚአብሔር ለእስራኤል በሰጠው ሕግ መሠረት፥ ዘወትር ጠዋትና ማታ በሙሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ እንዲያቃጥሉ ነው። 41በዚያም ከእነርሱ ጋር ሄማን፥ ይዱታን እንዲሁም የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊ ፍቅር በማሰብ ዘወትር ለእርሱ የምስጋና መዝሙር ያቀርቡ ዘንድ ሌሎችም በተለይ የተመረጡ ሰዎች ነበሩ፤ 42ሄማንና ይዱታን ለእምቢልታዎች፥ ለጸናጽሎችና የምስጋና መዝሙር ሲዘመር ለሚጠቀሙባቸው ሌሎች የዜማ ዕቃዎች ኀላፊዎች ሆኑ፤ የይዱቱን ልጆች አባሎች ለቅጽር በሮች ጥበቃ ኀላፊዎች ሆኑ።
43ከዚያም በኋላ ሰው ሁሉ ወደየቤቱ ሄደ፤ ዳዊትም ቤተሰቡን ለመባረክ ወደ ቤቱ ተመለሰ። #2ሳሙ. 6፥19-20።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997