የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 15

15
የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ የተደረገ ዝግጅት
1ዳዊት የሚኖርባቸውን ቤቶች በራሱ ከተማ በኢየሩሳሌም ሠራ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት የሚኖርበትንም ስፍራ አዘጋጅቶ ድንኳን ተከለለት፤ 2ከዚህም በኋላ ዳዊት እግዚአብሔር ለዘለዓለም እርሱን እንዲያገለግሉና የቃል ኪዳኑንም ታቦት እንዲሸከሙ የመረጣቸው እነርሱን ስለ ሆነ “የቃል ኪዳኑን ታቦት መሸከም የሚገባቸው ሌዋውያን ብቻ ናቸው” አለ። #ዘዳ. 10፥8። 3ስለዚህም ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደተዘጋጀለት ስፍራ ለመውሰድ የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም አስጠራ፤ 4ቀጥሎም የአሮንን ዘሮችና ሌዋውያንን አስጠራ፤ 5ከሌዋዊው ቀዓት ጐሣ፥ ኡሪኤል መቶ ኻያ ለሚሆኑት የጐሣው አባሎች ተጠሪ ሆኖ መጣ፤ 6ከመራሪ ጐሣ፥ ዐሣያ ሁለት መቶ ኻያ ለሚሆኑት የጐሣው አባሎች ተጠሪ ሆኖ መጣ፤ 7ከጌርሾን ጐሣ፥ ኢዮኤል መቶ ሠላሳ ለሚሆኑት የጐሣ አባሎች ተጠሪ ሆኖ መጣ፤ 8ከኤሊጻፋን ጐሣ፥ ሸማዕያ ሁለት መቶ ለሚሆኑት የጐሣ አባሎች ተጠሪ ሆኖ መጣ፤ 9ከኬብሮን ጐሣ፥ ኤሊኤል ሰማኒያ ለሚሆኑ የጐሣ አባሎች ተጠሪ ሆኖ መጣ፤ 10ከዑዚኤል ጐሣ፥ ዓሚናዳብ መቶ ዐሥራ ሁለት ለሚሆኑ የጐሣ አባሎች ተጠሪ ሆኖ መጣ።
11ዳዊት ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን እንዲሁም ኡሪኤልን፥ ዐሣያን፥ ኢዮኤልን፥ ሸማዕያን፥ ኤሊኤልንና ዓሚናዳብን በአጠቃላይ ስድስት ሌዋውያንን ወደ ድንኳን ውስጥ አስገባ። 12ሌዋውያኑንም እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ እናንተ ለሌዋውያን ጐሣዎች መሪዎች ናችሁ፤ የእስራኤል አምላክን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት እኔ ወዳዘጋጀሁለት ስፍራ ተሸክማችሁ ታመጡ ዘንድ ራሳችሁንና ሌዋውያን ወገኖቻችሁን ሁሉ ቀድሱ፤ 13ከዚህ በፊት እናንተ ተገኝታችሁ ታቦቱን ባለመሸከማችሁ በተደነገገው ሥርዓት መሠረት ስላላገለገልነው አምላካችን እግዚአብሔር ቀጥቶናል።”
14ከዚህ በኋላ የእስራኤል አምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸክመው ይወስዱ ዘንድ ካህናትና ሌዋውያን ራሳቸውን አነጹ፤ 15እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሌዋውያን ታቦቱን በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎች ተሸክመው ሄዱ። #ዘፀ. 25፥14።
16ዳዊት “በገና፥ መሰንቆና ጸናጽል በመሳሰሉ የሙዚቃ መሣሪያዎች እየታጀቡ የደስታ መዝሙሮችን ይዘምሩ ዘንድ ወንድሞቻችሁ የሆኑትን ሌዋውያንን ሹሙአቸው” በማለት የሌዋውያኑን መሪዎች ተናገረ፤ 17-21ከመዘምራን ጐሣ የነሐስ ጸናጽል የሚያንሿሹ የኢዮኤል ልጅ ሄማን፥ የእርሱ ዘመድ የሆነው የበራክያ ልጅ አሳፍ፥ እንዲሁም ከመራሪ ጐሣ የቁሳያ ልጅ ኤታን ተመረጡ፤ በከፍተኛ ድምፅ የሚደረደረውን በገና በመምታት የእነርሱ ረዳቶች እንዲሆኑም ዘካርያስ፥ ያዕዚኤል፥ ሸሚራሞት፥ ይሒኤል፥ ዑኒ፥ ኤሊአብ፥ ማዕሤያና በናያ ተመረጡ።
በዝቅተኛ ድምፅ የሚደረደረውን በገና እንዲመቱ ማቲትያ፥ ኤሊፈሌ፥ ሚቅኔያ፥ ዐዛዝያ እንዲሁም ከቤተ መቅደስ ዘበኞች መካከል ዖቤድኤዶምና ዩዒኤል ተብለው የሚጠሩት ሰዎች ተመረጡ።
22ከናንያ የሙዚቃ ችሎታ ስለ ነበረው ለሌዋውያኑ መዘምራን መሪ ሆኖ ተመረጠ፤ 23-24በራክያ፥ ኤልቃና፥ ዖቤድኤዶምና ዩሒያ የቃል ኪዳኑ ታቦት ጠባቂዎች ሆነው ተመረጡ፤ ካህናቱ ሸባንያ፥ ኢዮሣፍጥ፥ ናትናኤል፥ ዐማሣይ፥ ዘካርያስ፥ በናያና ኤሊዔዘር በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ፊት እየሄዱ እምቢልታ እንዲነፉ ተመረጡ።
የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መወሰዱ
(2ሳሙ. 6፥12-22)
25ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዳዊት፥ የእስራኤል ሕዝብ መሪዎችና የጦር አዛዦች የቃል ኪዳኑን ታቦት ለማምጣት ወደ ዖቤድኤዶም ቤት ሄዱ፤ ከፍ ያለ የደስታ ሥነ ሥርዓትም አደረጉ፤ 26የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትን ሌዋውያን እግዚአብሔር ስለ ረዳቸው ሰባት ኰርማዎችንና ሰባት በጎችን ሠዉ፤ 27ዳዊት ከጥሩ በፍታ የተሠራ መጐናጸፊያና ኤፉድ ለብሶ ነበር፤ እንዲሁም መዘምራኑ በሙሉ፥ የመዘምራኑ መሪ ከናንያና የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ሌዋውያን ከጥሩ በፍታ የተሠራ ልብስ ለብሰው ነበር። 28በዚህ ዐይነት መላው እስራኤላውያን ጥሩምባና እምቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽል እያንሿሹ፥ መሰንቆና በገና እየደረደሩ በሆታና በእልልታ የቃል ኪዳኑን ታቦት አጅበው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።
29ታቦቱ ወደ ከተማይቱ በመግባት ላይ ሳለ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ንጉሥ ዳዊት በደስታ ሲያሸበሽብና ሲዘል በመስኮት ተመለከተች፤ በልብዋም ናቀችው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ