የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 13

13
የቃል ኪዳኑን ታቦት ከቂርያትይዓሪም ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ መሞከሩ
(2ሳሙ. 6፥1-11)
1ንጉሥ ዳዊት የሻለቅነትና የመቶ አለቅነት ማዕርግ ካላቸው የጦር አለቆች ጋር ተመካከረ፤ 2ከዚያም በኋላ ለመላው የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ሲል አስታወቀ፥ “እናንተ ከተስማማችሁበትና የአምላካችን የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ፥ የቀሩት የአገራችን ሰዎች፥ ካህናትና ሌዋውያን ወደሚኖሩባቸው ታናናሽ ከተማዎች መልእክተኞች ልከን ወደዚህ መጥተው ከእኛ ጋር እንዲሰበሰቡ እንንገራቸው፤ 3በሳኦል ዘመነ መንግሥት ችላ ብለነው የነበረውንም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ሄደን እናመጣለን።” 4ሕዝቡም በሐሳቡ ደስ በመሰኘት ተስማሙ።
5ስለዚህም ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ከቂርያትይዓሪም ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት በደቡብ በኩል እስከ ግብጽ ግዛት ድንበር፥ በሰሜን እስከ ሐማት መተላለፊያ ድረስ በመላው እስራኤል የሚገኘውን ሕዝብ በአንድነት ሰበሰበ። #1ሳሙ. 7፥1-2። 6ዳዊትና ሕዝቡ ሁሉ በኪሩቤል ክንፎች ላይ የተቀመጠውን፥ በእግዚአብሔር ስም የተጠራውን የአምላካቸውን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ያመጡ ዘንድ በይሁዳ ግዛት ባዓላ ተብላ ወደምትጠራው ወደ ቂርያትይዓሪም ከተማ ሄዱ፤ #ዘፀ. 25፥22። 7የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአቢናዳብ ቤት አውጥተው በአዲስ ሠረገላ ላይ ጫኑት፤ ዑዛና አሕዮም ሠረገላውን ይነዱ ነበር፤ 8ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ መሰንቆና በገና እየደረደሩ፥ አታሞ እየመቱ፥ ጸናጽል እያንሿሹና እምቢልታ እየነፉ በመዘመር በሙሉ ኀይላቸው ለእግዚአብሔር ክብር ያሸበሽቡ ነበር።
9ወደ ኪዶንም አውድማ በደረሱ ጊዜ ሠረገላውን የሚጐትቱት በሬዎች ሲፋንኑ አደናቀፋቸው፤ ዑዛም እጆቹን ዘርግቶ የቃል ኪዳኑን ታቦት በመደገፍ ያዘ፤ 10ዑዛ ታቦቱን በመንካቱ እግዚአብሔር ተቈጥቶ ወዲያውኑ በሞት ቀሠፈው፤ ስለዚህም ዑዛ በዚያው በእግዚአብሔር ፊት ሞተ፤ 11ያም ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ “ፔሬጽ ዑዛ” ተብሎ ይጠራል፤ እግዚአብሔር ተቈጥቶ ዑዛን ስለ ገደለው ዳዊት እጅግ ተበሳጨ።
12ከዚህ በኋላ ዳዊት እግዚአብሔርን እጅግ ስለ ፈራ “እንግዲህ ይህን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤቴ እንዴት መውሰድ እችላለሁ?” አለ፤ 13ስለዚህም ዳዊት ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም በመውሰድ ፈንታ የጋት ከተማ ነዋሪ በሆነው፥ ዖቤድኤዶም ተብሎ በሚጠራው ሰው ቤት ተወው። 14ታቦቱም በዚያ ሦስት ወር ቈየ፤ እግዚአብሔርም የዖቤድኤዶምን ቤተሰብና የእርሱ የሆነውን ነገር ሁሉ ባረከ። #1ዜ.መ. 26፥4-5።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ