አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 12
12
ከብንያም ነገድ ቀደም ብለው ዳዊትን የተከተሉ ሰዎች
1ዳዊት ከቂስ ልጅ ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በጺቅላግ በነበረ ጊዜ ከእርሱ ጋር የተቀላቀሉት ሰዎች እነዚህ ናቸው፤ ከእነርሱም መካከል የጦር ጀግኖች ነበሩባቸው። 2እነርሱም ከብንያም ነገድ ስለ ነበሩ የሳኦል ዘመዶች ነበሩ፤ እነርሱ በቀኝና በግራ እጃቸው ፍላጻ የመወርወርና ድንጋይ የመወንጨፍ ችሎታ ያላቸው ነበሩ፤ 3-7እነርሱ የጊብዓ ተወላጅ የሆነው የኢሸማዓ ልጆች በሆኑት በአሒዔዜርና በዮአሽ አመራር ሥር ነበሩ። የወታደሮቹም ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ነው፦
የዓዝማዌት ልጆች ይዚኤልና ፔሌጥ፥
የዐናቶት ተወላጆች የሆኑት በራካና ኢዩ፥
ዝነኛ ወታደር የነበረው፥ በኋላም የሠላሳዎቹ ኀያላን መሪዎች ከሆኑት አንዱ የሆነው፥ የገባዖን ተወላጅ ዩሽማዕያ፥
የገዴራ ተወላጆች የሆኑት ይርመያ፥ ያሕዚኤል፥ ዮሐናንና ዮዛባድ፥
የሐሪፍ ተወላጆች የሆኑት ኤልዑዛይ፥ ያሪሞት፥ በዓልያ፥ ሸማርያና ሸፋጥያ፥
ከቆሬ ጐሣዎች የሆኑት ኤልቃና፥ ዩሺያሁ፥ ዐዛርኤል፥ ዮዔዜርና ያሸብዓም፥
የገዶር ተወላጆች የሆኑት የይሮሐም ልጆች ዮዔላና ዘባድያ።
ከጋድ ነገድ ዳዊትን የተከተሉ ሰዎች
8ዳዊት በበረሓ በሚገኘው ምሽግ ውስጥ ሳለ ከጋድ ነገድ መጥተው ከእርሱ ሠራዊት ጋር የተባበሩት ዝነኞችና የጦር ልምድ ያላቸው ወታደሮች ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው፤ እነርሱ ጋሻና ጦር ይዘው በመዋጋት የታወቁ ነበሩ፤ አስፈሪነታቸው እንደ አንበሳ ሲሆን ፈጣንነታቸው በተራራ ላይ እንደሚዘል ሚዳቋ ነበር፤ 9-13የእነርሱም ስም በሚከተለው ሁኔታ በየማዕርጋቸው በቅደም ተከተል ተራ ተዘርዝሮአል፦ ዔዜር፥ አብድዩ ኤሊአብ፥ ሚሽማና፥ ኤርምያስ፥ ዓታይ፥ ኤሊኤል፥ ዮሐናን፥ ኤልዛባድ፥ ኤርምያስ ማክባናይ።
14ከጋድ ነገድ ከሆኑት ከእነዚህ ሰዎች መካከል ጥቂቶቹ የሺህ አለቅነት ማዕርግ ያላቸው የበላይ መኰንኖችና የመቶ አለቅነት ማዕርግ ያላቸው የበታች መኰንኖች ነበሩ። 15እነዚህም የጋድ ነገድ አባሎች በአንድ ወቅት የዓመቱ የመጀመሪያ ወር እንደ ገባ፥ የዮርዳኖስም ወንዝ ከአፍ እስከ ገደፍ ሞልቶ ሳለ ወንዙን ተሻገሩ፤ ከወንዙ በሰተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ በሸለቆዎቹ ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን ሰዎች አባረሩ።
ከብንያምና ከይሁዳ ነገዶች ዳዊትን የተከተሉ ሰዎች
16አንድ ጊዜ ከይሁዳና ከብንያም ነገዶች የተውጣጡ ጥቂት ሰዎች ዳዊት ወዳለበት ምሽግ ሄዱ፤ 17ዳዊትም ወደ እነርሱ ቀርቦ እንዲህ አላቸው፤ “ወደዚህ የመጣችሁት በወዳጅነት ልትረዱኝ ከሆነ መልካም ነው፤ በደስታ እቀበላችኋለሁ፤ ከእኛም ጋር ሁኑ! እኔ ምንም ሳላደርጋችሁ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ ከሆነ ግን የቀድሞ አባቶቻችን አምላክ ተመልክቶ ይፍረደው።”
18የእግዚአብሔር መንፈስ የሠላሳዎቹ
መሪ በሆነው በዐማሳይ ላይ ወረደ፤ እርሱም፦
“ዳዊት ሆይ! እኛ የአንተ ነን!
የእሴይ ልጅ ዳዊት ሆይ! እኛ ከአንተ ጋር ነን!
ለአንተና አንተን ለሚረዱ ሁሉ ሰላም ይሁን!
እግዚአብሔር ከአንተ ጋር በመሆን ይረዳሃል፤”
በማለት ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸ፤ ዳዊትም እነርሱን በደስታ ተቀብሎ በሠራዊቱ ውስጥ አለቆች አደረጋቸው።
ከምናሴ ነገድ ዳዊትን የተከተሉ ሰዎች
19ዳዊት፥ ንጉሥ ሳኦልን ለመውጋት ከፍልስጥኤማውያን ጋር በዘመተ ጊዜ ከምናሴ ነገድ የሆኑ ጥቂት ወታደሮች ከዳዊት ጋር ለመተባበር ሄዱ፤ ሆኖም የፍልስጥኤማውያን መሪዎች “ዳዊት እኛን ከድቶ ወደ ቀድሞ ጌታው ወደ ሳኦል ይመለሳል” ብለው ስለ ፈሩ ከተመካከሩ በኋላ ወደ ቲግላግ እንዲመለስ አደረጉት፤ 20ከምናሴ ነገድ ዳዊት በተመለሰ ጊዜ ወደ እርሱ የሄዱት ወታደሮች ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ነው፦ ዓድናሕ፥ ዮዛባድ፥ ይዲዕኤል፥ ሚካኤል፥ ዮዛባድ፥ ኤሊሁና ጺለታይ፤ እነዚህ ሁሉ በምናሴ ግዛት ሳሉ የሺህ አለቅነት ማዕርግ የነበራቸው ናቸው። 21ሁሉም ዝነኞች ወታደሮች ነበሩ። የጠላት ወታደሮች በሚያጠቁበት ጊዜ ዳዊትን ይረዱ ነበር፤ በሠራዊቱም ውስጥ የጦር አለቆች ሆነዋል። 22በየቀኑ አዳዲስ ሰዎች ወደ ዳዊት ሠራዊት እየመጡ ይቀላቀሉ ስለ ነበር ብዙ ሳይቈይ የዳዊት ሠራዊት እጅግ የበዛና ኀያል ሆነ።
የዳዊት ሠራዊት ብዛት
23-37ዳዊት በኬብሮን ሳለ ብዙ የሠለጠኑ ወታደሮች ወደ እርሱ ሠራዊት ገቡ፤ እግዚአብሔር በሰጠውም የተስፋ ቃል መሠረት በሳኦል እግር ተተክቶ እንዲነግሥ ብዙ ርዳታ አደረጉለት፤ ቊጥራቸውም እንደሚከተለው ነበር፦
ከይሁዳ ነገድ፦ ጋሻና ጦር በሚገባ የታጠቁ ስድስት ሺህ ስምንት መቶ ወታደሮች፥
ከስምዖን ነገድ፦ በሚገባ የሠለጠኑ ሰባት ሺህ አንድ መቶ ወታደሮች፥
ከሌዊ ነገድ፦ አራት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች፤
የአሮን ዘሮች የሆኑት የዮዳሄ ተከታዮች ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች፥
ታዋቂ ጦረኛ ከሆነው ከጻዶቅ ዘመዶች፦ ኻያ ሁለት የጦር አዛዦች፥
የሳኦል ወገን ከሆነው ከብንያም ነገድ፦ ሦስት ሺህ ሰዎች፤ ይሁን እንጂ ከብንያም ነገድ አብዛኛው ሕዝብ ለሳኦል ያላቸውን ታማኝነት እንደ ቀጠሉ ነበሩ።
ከኤፍሬም ነገድ፦ ኻያ ሺህ ስምንት መቶ ሰዎች ሲሆኑ፥ ሁሉም በየጐሣቸው ዝነኞች የሆኑ ጀግኖች ነበሩ።
በምዕራብ በኩል ካለው ከምናሴ ነገድ፦ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች ሲሆኑ፥ እነርሱም ዳዊትን ለማንገሥ በተለይ የተመረጡ ናቸው።
ከይሳኮር ነገድ፦ ሁለት መቶ መሪዎች ሲሆኑ፥ በእነርሱ አመራር ሥር ያሉትንም ያጠቃልላል፤ እነዚህ መሪዎች እስራኤል ምን ማድረግና መቼ ማድረግ እንደሚገባት የሚያውቁ ናቸው።
ከዛብሎን ነገድ፦ እምነት የሚጣልባቸው ለጦርነት ዝግጁዎች የሆኑ በማንኛውም መሣሪያ መጠቀም የሚችሉ ኀምሳ ሺህ ወታደሮች፤
ከንፍታሌም ነገድ፦ አንድ ሺህ የጦር መሪዎችና ጋሻና ጦር ያነገቡ ሠላሳ ሰባት ሺህ ወታደሮች ነበሩ።
ከዳን ነገድ፦ ኻያ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ የሠለጠኑ ወታደሮች ነበሩ።
ከአሴር ነገድ፦ አርባ ሺህ ለጦርነት የተዘጋጁ ወታደሮች ነበሩ።
ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ካሉት ከሮቤል፥ ከጋድና ከምናሴ ነገዶች፦ በማንኛውም ዐይነት መሣሪያ የመጠቀም ችሎታ ያላቸው አንድ መቶ ኻያ ሺህ ወታደሮች ነበሩ።
38እነዚህ ሁሉ ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ወታደሮች ዳዊትን በመላው እስራኤል ላይ ለማንገሥ ቊርጥ ውሳኔ አድርገው ወደ ኬብሮን ሄዱ፤ የቀሩትም እስራኤላውያን በዚሁ ዓላማ በአንድነት ተስማምተው ነበር፤ 39እነዚህ ሁሉ የገዛ ወገኖቻቸው ያዘጋጁላቸውን በደስታ እየተመገቡና እየጠጡ፥ ሦስት ቀን ከዳዊት ጋር ቈዩ፤ 40በስተ ሰሜን በኩል ካሉት ከይሳኮር፥ ከዛብሎንና ከንፍታሌም ነገዶች ሳይቀር ብዙ ሰዎች በአህያ፥ በግመል፥ በበቅሎና በበሬ ብዙ ምግብ፥ ዱቄት፥ በለስ፥ ዘቢብ፥ የወይን ጠጅና የወይራ ዘይት በመጫን ይዘው መጥተው ነበር፤ እንዲሁም ዐርደው የሚበሉአቸውን ብዙ የቀንድ ከብቶችና በጎችን ይዘው መጥተዋል፤ ይህም ሁሉ በመላው አገሪቱ ላይ የሚገኘው ሕዝብ የተሰማውን ደስታ የሚገልጥ ነበር።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 12: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997