የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 11:1-9

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 11:1-9 አማ05

እስራኤላውያን ሁሉ በኬብሮን ወደነበረው ወደ ዳዊት ሄደው እንዲህ አሉት፦ “እኛ ሁላችን የሥጋ ዘመዶችህ ነን፤ ባለፉት ዘመናት ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሳለ እንኳ የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ጦርነት የምትመራ አንተ ነበርክ፤ ‘ሕዝቤን እስራኤልን የምትመራና የምታስተዳድር አንተ ነህ’ ብሎ አምላክህ እግዚአብሔር ነግሮሃል።” በዚያም ዐይነት የእስራኤል መሪዎች ሁሉ በኬብሮን ወደነበረው ወደ ንጉሥ ዳዊት መጡ፤ እርሱም ከእነርሱ ጋር የተቀደሰ ስምምነት አደረገ፤ እግዚአብሔር በሳሙኤል አማካይነት በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት ሕዝቡ ዳዊትን ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት። ንጉሥ ዳዊትና መላው የእስራኤል ሕዝብ ሄደው በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ አደጋ ጣሉ፤ በዚያን ጊዜ የከተማይቱ ስም “ኢያቡስ” ይባል ነበር፤ በምድሪቱ ላይ ይኖሩ የነበሩት ኢያቡሳውያን ናቸው። ኢያቡሳውያን ዳዊትን “ከቶ ወደዚህ አትገባም” አሉት፤ ዳዊት ግን በጽዮን የሠሩትን ምሽጋቸውን ያዘ፤ ከዚያም በኋላ ያቺ ስፍራ “የዳዊት ከተማ” ተብላ ትጠራ ጀመር። ዳዊትም “በመጀመሪያ በኢያቡሳውያን ላይ አደጋ የሚጥል ሰው የሠራዊቱ አዛዥ ይሆናል!” አለ፤ የጸሩያ ልጅ ኢዮአብ በመጀመሪያ ሄዶ በኢያቡሳውያን ላይ አደጋ በመጣሉ የሠራዊቱ አዛዥ ሆነ፤ ዳዊትም ሄዶ በምሽጉ ውስጥ ስለ ኖረ ያቺ ስፍራ “የዳዊት ከተማ” ተብላ ተጠራች። ዳዊት ከኰረብታው በስተ ምሥራቅ በኩል በዐፈር ከተደለደለው ስፍራ አንሥቶ ከተማይቱን እንደገና ሠራ፤ ኢዮአብም በበኩሉ የቀረውን የከተማይቱን ክፍል ሠራ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በመሆኑ ዳዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ።