ማሕልየ መሓልይ 6
6
ባልንጀሮቿ
1አንቺ ከሴቶች ሁሉ የተዋብሽ ሆይ፤
ውድሽ ወዴት ሄደ?
ዐብረንሽም እንድንፈልገው፣
ውድሽ የሄደው በየት በኩል ነው?
ሙሽራዪቱ
2ውዴ መንጋውን ለማሰማራት፣
ውብ አበቦችንም ለመሰብሰብ፣
የቅመማ ቅመም መደቦቹ ወዳሉበት፣
ወደ አትክልት ቦታው ወርዷል።
3እኔ የውዴ ነኝ፤ ውዴም የእኔ ነው፤
መንጋውንም በውብ አበቦች መካከል ያሰማራል።
ሙሽራው
4ውዴ ሆይ፤ አንቺ እንደ ቴርሳ የተዋብሽ፣
እንደ ኢየሩሳሌም ያማርሽ፣
ዐርማቸውን እንደ ያዙ ወታደሮችም ግርማን የተጐናጸፍሽ ነሽ።
5አስጨንቀውኛልና፣
እባክሽ ዐይኖችሽን ከእኔ ላይ አንሺ፤
ጠጕርሽ ከገለዓድ ተራራ የሚወርድ፣
የፍየል መንጋ ይመስላል።
6ጥርሶችሽ
ከመታጠቢያ እንደ ወጡ የበግ መንጋ ናቸው፤
ሁሉም መንታ መንታ የወለዱ፣
ከመካከላቸውም መካን የሌለባቸው ናቸው።
7ከመሸፈኛሽ ውስጥ ያሉት ጕንጮችሽ፣
ለሁለት የተከፈለ ሮማን ይመስላሉ።
8ስድሳ ንግሥቶች፣
ሰማንያ ቁባቶች፣
ቍጥራቸውም የበዛ ደናግል ሊኖሩ ይችላሉ፤
9እንከን የሌለባት ርግቤ ግን ልዩ ናት፤
እርሷ ለወለደቻት የተመረጠች፣
ለእናቷም አንዲት ናት፤
ቈነጃጅት አይተው “የተባረክሽ ነሽ”
አሏት፤
ንግሥቶችና ቁባቶችም አመሰገኗት።
ባልንጀሮቿ
10እንደ ንጋት ብርሃን ብቅ የምትል፣
እንደ ጨረቃ የደመቀች፣ እንደ ፀሓይ ያበራች፣
ዐርማ ይዞ በሰልፍ እንደ ወጣ ሰራዊት ግርማዋ የሚያስፈራ ይህች ማን ናት?
ሙሽራው
11በሸለቆው ውስጥ አዲስ የበቀሉትን አትክልቶች ለማየት፣
ወይኑ ማቈጥቈጡን፣
ሮማኑ ማበቡን ለመመልከት፣
ወደ ለውዙ ተክል ቦታ ወረድሁ።
12ይህን ከማወቄ በፊት፣
ምኞቴ በሕዝቤ ንጉሣዊ ሠረገሎች መካከል#6፥12 ወይም ከአሚናዳብ ሠረገሎች መካከል ወይም ከልዑል ሕዝቦች ሠረገሎች መካከል አስቀመጠኝ።
ባልንጀሮቿ
13አንቺ ሱላማጢስ ሆይ፤ ተመለሺ፤
ኧረ ተመለሺ፤ እንድናይሽ ተመለሺ፤ እባክሽ ተመለሺ።
ሙሽራው
የመሃናይምን ዘፈን እንደሚመለከት ሰው፣
ሱላማጢስን የምትመለከቷት ለምንድን ነው?
Currently Selected:
ማሕልየ መሓልይ 6: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.