የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሩት 3:1-18

ሩት 3:1-18 NASV

ከዚህ በኋላ ዐማቷ ኑኃሚን ሩትን እንዲህ አለቻት፤ “ልጄ ሆይ፤ የሚመችሽን ቤት እንድፈልግልሽ አይገባኝምን? ከሴቶች ሠራተኞቹ ጋር አብረሽ የነበርሽበት ቦዔዝ፣ ዘመዳችን አይደለምን? ዛሬ ማታ በዐውድማው ላይ ገብስ ያበራያል፤ ተጣጠቢ፤ ሽቶ ተቀቢ፤ እንዲሁም የክት ልብስሽን ልበሺ፤ ከዚያም ወደ ዐውድማው ውረጂ፤ ይሁን እንጂ በልቶና ጠጥቶ እስኪያበቃ ድረስ፣ እዚያ መሆንሽን እንዳያውቅ ይሁን። በተኛም ጊዜ፣ የሚተኛበትን ቦታ ልብ ብለሽ እዪና ሄደሽ እግሩን ገልጠሽ ተኚ፤ ከዚያም የምታደርጊውን ራሱ ይነግርሻል።” ሩትም፣ “ያልሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አለቻት። ስለዚህ ተነሥታ ወደ ዐውድማው ወረደች፤ ዐማቷ አድርጊ ያለቻትንም ሁሉ አደረገች። ቦዔዝ በልቶ ጠጥቶ ከጨረሰና ደስም ከተሰኘ በኋላ፣ ራቅ ካለው የእህል ክምር አጠገብ ለመተኛት ሄደ። ሩት በቀስታ ከአጠገቡ ደረሰች፤ እግሩንም ገልጣ ተኛች። እኩለ ሌሊት ላይ ሰውየውን አንዳች ነገር አስደነገጠው፤ ገልበጥ ሲልም አንዲት ሴት እግርጌው ተኝታ አገኘ። እርሱም፣ “አንቺ ማነሽ?” ሲል ጠየቀ። እርሷም፣ “እኔ አገልጋይህ ሩት ነኝ፤ መቤዠት የሚገባህ ቅርብ የሥጋ ዘመድ አንተ ነህና ልብስህን ጣል አድርግብኝ” አለችው። እርሱም መልሶ እንዲህ አላት፤ “ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሔር ይባርክሽ፤ ከዚህ በፊት ካደረግሽው ይልቅ ያሁኑ በጎነትሽ ይበልጣል፤ ባለጠጋም ሆነ ድኻ፣ ወጣት ወንድ ፈልገሽ አልሄድሽምና። አሁንም ልጄ ሆይ፤ አትፍሪ፤ የምትጠይቂውን ሁሉ አደርግልሻለሁ፤ አንቺ ምግባረ መልካም ሴት መሆንሽንም የአገሬ ሰው ሁሉ ያውቀዋል። ምንም እንኳ እኔ ቅርብ የሥጋ ዘመድ መሆኔ የተረጋገጠ ቢሆንም፣ ከእኔ ይልቅ መቤዠት የሚገባው ቅርብ የሥጋ ዘመድ አለ። ከዚህ ዕደሪ፤ ሲነጋም ሰውየው ሊቤዥሽ ከፈለገ፣ መልካም ነው፤ ይቤዥሽ፤ የማይፈልግ ከሆነ ግን በሕያው እግዚአብሔር እምላለሁ፤ እኔ እቤዥሻለሁ፤ እስኪነጋም ድረስ እዚሁ ተኚ።” ስለዚህም ሩት እስኪነጋ ድረስ እግርጌው ተኛች፤ ዳሩ ግን ማንም ሰው ተለይቶ ሊታወቅ በማይችልበት ሰዓት ቀደም ብላ ተነሣች፤ እርሱም፣ “ሴት ወደዚህ ዐውድማ መምጣቷ እንዳይታወቅ” አላት። እንዲሁም፣ “በላይሽ የደረብሽውን ልብስ አቅርቢልኝ፤ ዘርግተሽም ያዢው” አላት፤ ዘርግታ እንደ ያዘችም ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰፍሮ አሸከማት፤ ከዚያም ወደ ከተማ ተመለሰች። ሩት ወደ ዐማቷ እንደ ተመለሰች፣ ኑኃሚን፣ “ልጄ ሆይ፤ የሄድሽበት ጕዳይ እንዴት ሆነ?” ብላ ጠየቀቻት። ሩትም ቦዔዝ ያደረገላትን ሁሉ ነገረቻት፤ ቀጥላም፣ “ ‘ወደ ዐማትሽ ባዶ እጅሽን አትመለሺ’ በማለት ይህን ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰጠኝ” አለቻት። ኑኃሚንም፣ “ልጄ ሆይ፤ የሚሆነውን ነገር እስክታውቂ ድረስ ታገሺ፤ ጕዳዩ ዛሬውኑ እልባት ካላገኘ ሰውየው አያርፍም” አለቻት።