ኑኃሚን፣ ከአቤሜሌክ ጐሣ የሆነ ቦዔዝ የሚባል ባለ ጸጋ የባል ዘመድ ነበራት። ሞዓባዊቷ ሩትም ኑኃሚንን፣ “በፊቱ ሞገስ አግኝቼ ቃርሚያ የሚያስቃርመኝ ሰው ባገኝ እስቲ ወደ እህል አዝመራው ልሂድ” አለቻት። ኑኃሚንም፣ “ልጄ ሆይ፤ ይሁን ሂጂ” አለቻት። ስለዚህ እርሷም ወጣች፤ ከዐጫጆች ኋላ ኋላ እየተከታተለችም ከአዝመራው ቦታ ትቃርም ጀመር፤ እንዳጋጣሚ ትቃርምበት የነበረው አዝመራ ከአቤሜሌክ ጐሣ የሆነው የቦዔዝ ነበር። በዚሁ ጊዜ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፤ ዐጫጆቹንም፣ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን!” ብሎ ሰላምታ ሰጣቸው። እነርሱም፣ “እግዚአብሔር ይባርክህ!” ብለው መለሱለት። ከዚያም ቦዔዝ የዐጫጆቹን አለቃ፣ “ይህች ወጣት ሴት የማን ናት?” ሲል ጠየቀው። የዐጫጆቹም አለቃ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከኑኃሚን ጋር ከሞዓብ ምድር ተመልሳ የመጣች ሞዓባዊት ናት። እርሷም፣ ‘ዐጫጆቹን እየተከተልሁ በነዶው መካከል እንድቃርም እባክህ ፍቀድልኝ’ አለችኝ። ለጥቂት ጊዜ በመጠለያው ከማረፏ በስተቀር፣ ወደ አዝመራው ቦታ ገብታ ከጧት አንሥቶ እስካሁን ያለ ማቋረጥ ስትቃርም ቈይታለች።” ስለዚህም ቦዔዝ ሩትን፣ “ልጄ ሆይ ስሚኝ፤ ከእንግዲህ ወደ ሌላ አዝመራ ሄደሽ አትቃርሚ፤ ከዚህም አትራቂ፤ ከሴቶች ልጆቼ ጋር እዚሁ ሁኚ። ወንዶቹ የሚያጭዱበትን ዕርሻ ልብ እያልሽ ልጃገረዶቹን ተከተዪ፤ ወንዶቹ እንዳያስቸግሩሽም አስጠንቅቄአቸዋለሁ፤ ውሃ ሲጠማሽ ደግሞ፣ እየሄድሽ ወንዶቹ ሞልተው ካስቀመጡት እንስራ ቀድተሽ ጠጪ።” በዚህ ጊዜ ወደ መሬት ዝቅ ብላ እጅ ነሣችው። እርሷም፣ “ባይተዋር የሆንሁትን እኔን ታስበኝ ዘንድ በፊትህ ሞገስ ለማግኘት የበቃሁት እንዴት ነው?” አለችው። ቦዔዝም መልሶ እንዲህ አላት፤ “ባልሽ ከሞተ ጀምሮ ለዐማትሽ ያደረግሽላትን ሁሉ፣ አባት እናትሽን እንዲሁም የተወለድሽበትን አገር ትተሽ ቀድሞ ከማታውቂው ሕዝብ ጋር ለመኖር እንዴት እንደ መጣሽ ነግረውኛል። ስላደረግሽው ሁሉ እግዚአብሔር ዋጋሽን ይክፈልሽ፤ በክንፉ ጥላ ሥር ለመጠለል የመጣሽበት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ብድራትሽን አትረፍርፎ ይመልስልሽ።”
ሩት 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ሩት 2
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሩት 2:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos