የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሮሜ 4:13-25

ሮሜ 4:13-25 NASV

እርሱ የዓለም ወራሽ እንዲሆን አብርሃምና ዘሩ ተስፋን የተቀበሉት በሕግ በኩል አልነበረም፤ ነገር ግን በእምነት ከሆነው ጽድቅ ነው። በሕግ የሚኖሩት ወራሾች ከሆኑ፣ እምነት የማይጠቅም፣ ተስፋም ከንቱ በሆነ ነበር፤ ሕግ ቍጣን ያስከትላል፤ ሕግ በሌለበት ግን መተላለፍ አይኖርም። ስለዚህ ተስፋው በእምነት መጥቷል፤ ይኸውም ተስፋው በጸጋ እንዲሆንና ለአብርሃም ዘር ሁሉ ዋስትና ይሆን ዘንድ ነው፤ ይህም በሕግ የርሱ ለሆኑት ብቻ ሳይሆን፣ በእምነት የአብርሃም ለሆኑትም ነው፤ እርሱም የሁላችን አባት ነው። ይህም “የብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው፤ እርሱም ለሙታን ሕይወትን በሚሰጥ፣ ያልነበረውንም እንደ ነበረ በሚያደርግ፣ ባመነበት አምላክ ፊት አባታችን ነው። “ዘርህም እንዲሁ ይሆናል” ተብሎ ለርሱ በተነገረው መሠረት፣ ምንም ተስፋ በሌለበት፣ አብርሃም በተስፋ አምኖ የብዙ ሕዝብ አባት ሆነ። እርሱ የመቶ ዓመት ሰው ሆኖ ሳለ፣ የራሱም ሰውነት ሆነ የሣራ ማሕፀን ምዉት እንደ ነበረ እያወቀ በእምነቱ አልደከመም። ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም፤ እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም በሙሉ ልብ ርግጠኛ ነበር። ስለዚህ፣ “ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት።” “ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው ቃል የተጻፈው ለርሱ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ጽድቅ አድርጎ ለሚቈጥርልን፣ ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው በርሱ ለምናምን ለእኛም ጭምር ነው። እርሱ ስለ ኀጢአታችን እንዲሞት ዐልፎ ተሰጠ፤ እኛን ጻድቅ አድርጎ ለማቅረብም ከሞት ተነሣ።