እንግዲህ ምን እንላለን? እኛ ከእነርሱ እንበልጣለንን? ከቶ አይደለም፤ አይሁድም ሆኑ አሕዛብ፣ ሁሉም ከኀጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከስሰናቸዋል። እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ “ጻድቅ ማንም የለም፤ አንድ እንኳ፤ አስተዋይ የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚሻ አንድም የለም። ሁሉም ተሳስተዋል፤ በአንድነት የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ መልካም የሚያደርግ የለም፤ አንድ እንኳ።” “ጕረሯቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ይሸነግላሉ።” “በከንፈሮቻቸው የእባብ መርዝ አለ።” “አፋቸው ርግማንና ምሬት ሞልቶበታል።” “እግሮቻቸው ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፤ በመንገዶቻቸው ጥፋትና ጕስቍልና ይገኛሉ፤ የሰላምንም መንገድ አያውቁም።” “በዐይናቸው ፊት ፈሪሀ እግዚአብሔር የለም።” እንግዲህ አፍ ሁሉ እንዲዘጋና ዓለም በሙሉ ለእግዚአብሔር መልስ እንዲሰጥ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደ ሆነ፣ እናውቃለን፤ ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ማንም ሥጋ ለባሽ በርሱ ፊት ሊጸድቅ አይችልም፤ ይልቁንም በሕግ አማካይነት ኀጢአትን እንገነዘባለን። አሁን ግን ሕግና ነቢያት የመሰከሩለት፣ ከሕግ ውጭ የሆነ፣ የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጧል። ይህ የእግዚአብሔር ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን የሚገኝ ጽድቅ ነው። ልዩነት የለም፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሏቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት እንዲያው በጸጋው ጸድቀዋል፤ በደሙም በሆነው እምነት፣ እግዚአብሔር የማስተሰረያ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል፤ ይህንም ያደረገው ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ በትዕግሥት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው፤ በአሁኑ ዘመን እግዚአብሔር ይህን ያደረገው፣ ጽድቁን ይኸውም እርሱ ራሱ ጻድቅ ሆኖ፣ በኢየሱስ የሚያምነውን የሚያጸድቅ መሆኑን ለማሳየት ነው። ታዲያ ትምክሕት ወዴት ነው? እርሱማ ቀርቷል። በየትኛው ሕግ? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፤ በእምነት ሕግ ነው እንጂ። ማንም ሰው ሕግን በመፈጸም ሳይሆን፣ በእምነት እንደሚጸድቅ እናረጋግጣለን።
ሮሜ 3 ያንብቡ
ያዳምጡ ሮሜ 3
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሮሜ 3:9-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች