ራእይ 4
4
በሰማይ ያለው ዙፋን
1ከዚህ በኋላ እነሆ፤ በሰማይ የተከፈተ በር አየሁ፤ ቀደም ሲል እንደ መለከት ሲናገረኝ የሰማሁት ድምፅ፣ “ወደዚህ ና፤ ከዚህም በኋላ ሊሆን የሚገባውን ነገር አሳይሃለሁ” አለኝ። 2እኔም ወዲያወኑ በመንፈስ ነበርሁ፤ እነሆም በሰማይ ዙፋን ቆሟል፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠ ነበረ። 3ተቀምጦም የነበረው የኢያስጲድንና የሰርዲኖን ዕንይመስል ነበር። የመረግድ ዕንየመሰለ ቀስተ ደመናም ዙፋኑን ከብቦት ነበር። 4በዙፋኑ ዙሪያ ሌሎች ሃያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፤ በእነርሱም ላይ ነጭ ልብስ የለበሱና በራሳቸውም ላይ የወርቅ አክሊል የደፉ ሃያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር። 5ከዙፋኑም መብረቅና ድምፅ፣ ነጐድጓድም ወጣ፤ በዙፋኑ ፊት ሰባት መብራቶች ይበሩ ነበር፤ እነዚህም ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት#4፥5 ወይም ሰባት ዕጥፍ መንፈስ ናቸው። 6ደግሞም በዙፋኑ ፊት እንደ መስተዋት የጠራ የብርጭቆ ባሕር ነበረ።
በዙፋኑ መካከል፣ በዙሪያውም ከፊትና ከኋላ በዐይን የተሞሉ አራት ሕያዋን ፍጡራን ነበሩ። 7የመጀመሪያው ሕያው ፍጡር አንበሳ፣ ሁለተኛው በሬ ይመስሉ ነበር፤ ሦስተኛው የሰው ፊት የሚመስል ፊት ነበረው፤ አራተኛው ደግሞ የሚበርር ንስር ይመስል ነበር። 8አራቱም ሕያዋን ፍጡራን እያንዳንዳቸው ስድስት ስድስት ክንፎች ነበሯቸው፤ በዙሪያቸውና በውስጣቸው በዐይኖች የተሞሉ ነበሩ፤ ቀንና ሌሊትም፦
“ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣
የነበረው፣ ያለውና የሚመጣው፤
ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ”
ማለትን አያቋርጡም። 9ሕያዋን ፍጡራኑ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ከዘላለም እስከ ዘላለም ሕያው ሆኖ ለሚኖረው ክብር፣ ሞገስና ምስጋና በሚሰጡበት ጊዜ፣ 10ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ፊት ተደፍተው፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ሕያው ሆኖ ለሚኖረው ይሰግዱ ነበር፤ አክሊላቸውንም በዙፋኑ ፊት አስቀምጠው እንዲህ ይላሉ፤
11“ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤
ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤
አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤
በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤
ሆነዋልምና።”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.