የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 20:4-15

ራእይ 20:4-15 NASV

ቀጥሎም ዙፋኖችን አየሁ፤ በዙፋኖቹም ላይ ለመፍረድ ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎች ተቀምጠው ነበር፤ ደግሞም ስለ ኢየሱስ ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል የተሰየፉትን ሰዎች ነፍሶች አየሁ። እነርሱ ለአውሬው ወይም ለርሱ ምስል አልሰገዱም፤ በግንባራቸው ወይም በእጃቸው ላይ የአውሬውን ምልክት አልተቀበሉም፤ እነርሱም ከሞት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋራ ሺሕ ዓመት ነገሡ። የቀሩት ሙታን ግን ሺሑ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ከሞት አልተነሡም። ይህ የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው። በመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሚሆኑ ብፁዓንና ቅዱሳን ናቸው። ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከርሱም ጋራ ሺሕ ዓመት ይነግሣሉ። ሺሑም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤ በአራቱ የምድር ማእዘናት ያሉትን ሕዝቦች፣ ጎግንና ማጎግን እያሳተ ለጦርነት ሊያሰልፋቸው ይወጣል። ቍጥራቸው በባሕር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ነው። እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ ወጥተው የቅዱሳንን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ ነገር ግን እሳት ከሰማይ ወርዶ በላቸው። ያሳታቸው ዲያብሎስም፣ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ እነርሱም ቀንና ሌሊት ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሠቃያሉ። ከዚህ በኋላ ታላቅ ነጭ ዙፋንና በርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ። ምድርና ሰማይ ከፊቱ ሸሹ፤ ስፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። ሌላም መጽሐፍ፣ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ተከፈተ፤ ሙታንም በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው መሠረት እንደ ሥራቸው መጠን ተፈረደባቸው። ባሕርም በውስጡ የነበሩትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ውስጥ የነበሩትን ሙታን ሰጡ፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተፈረደበት። ከዚያም በኋላ ሞትና ሲኦል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ፤ የእሳቱ ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው። ስሙ በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ወደ እሳት ባሕር ተጣለ።