የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 2:18-29

ራእይ 2:18-29 NASV

“በትያጥሮን ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዐይኖችና በእሳት ቀልጦ የነጠረ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል። ሥራህን፣ ፍቅርህን፣ እምነትህን፣ አገልግሎትህንና ትዕግሥትህን ዐውቃለሁ፤ ደግሞም ከመጀመሪያው ሥራህ ይልቅ የአሁኑ እንደሚበልጥ ዐውቃለሁ። ይሁን እንጂ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ነቢይ ነኝ የምትለዋን ሴት ኤልዛቤልን ችላ ብለሃታል፤ እርሷ ባሮቼ እንዲሴስኑና ለጣዖት የተሠዋ ምግብ እንዲበሉ በትምህርቷ ታስታቸዋለች። ከዝሙቷ ንስሓ እንድትገባ ጊዜ ሰጥቻት ነበር፤ እርሷ ግን ፈቃደኛ አልሆነችም። ስለዚህ በመከራ ዐልጋ ላይ እጥላታለሁ፤ ከርሷም ጋራ የሚያመነዝሩትን፣ ከመንገዷ ንስሓ ካልገቡ፣ ብርቱ ሥቃይ አመጣባቸዋለሁ፤ ልጆቿንም በሞት እቀጣቸዋለሁ። ከዚያም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እኔ ልብንና ሐሳብን የምመረምር መሆኔን ይረዳሉ፤ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እከፍላችኋለሁ። ትምህርቷን ላልተከተላችሁና የሰይጣንም ጥልቅ ምስጢር ነው የሚባለውን ላልተቀበላችሁ፣ በትያጥሮን ለቀራችሁት ለእናንተ ግን ይህን እላለሁ፤ በእናንተ ላይ ተጨማሪ ሸክም አልጭንባችሁም፤ ብቻ እኔ እስክመጣ ድረስ ያላችሁን አጥብቃችሁ ያዙ። ድል ለሚነሣና ሥራዬንም እስከ መጨረሻው ለሚፈጽም በአሕዛብ ላይ ሥልጣን እሰጠዋለሁ፤ እርሱም፦ ‘በብረት በትር ይገዛቸዋል፤ እንደ ሸክላ ዕቃም ይፈጫቸዋል፤’ ይህም ልክ እኔ ከአባቴ ዘንድ ሥልጣንን እንደ ተቀበልሁ ነው፤ እኔም የንጋትን ኮከብ እሰጠዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።