ደግሞም እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ፣ እንደ ኀይለኛ ወራጅ ውሃ ድምፅ፣ እንደ ብርቱም ነጐድጓድ ድምፅ የሚመስል እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሃሌ ሉያ! ሁሉን ቻይ ጌታ አምላካችን ነግሧልና። የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ፣ የእርሱም ሙሽራ ራሷን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን፤ ሐሤት እናድርግ፤ ክብርም እንስጠው። የሚያንጸባርቅና ንጹሕ፣ ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ እንድትለብስ ተሰጣት።” ከተልባ እግር የተሠራው ቀጭን ልብስ የቅዱሳን የጽድቅ ሥራ ነው። መልአኩም፣ “ ‘ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው’ ብለህ ጻፍ” አለኝ፤ ቀጥሎም፣ “እነዚህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃሎች ናቸው” አለኝ። እኔም ልሰግድለት በእግሩ ሥር ተደፋሁ፤ እርሱ ግን፣ “ተው! ይህን አታድርግ! እኔም ከአንተና የኢየሱስን ምስክር ከያዙት ወንድሞችህ ጋራ አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና” አለኝ። ከዚያም ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆ አንድ ነጭ ፈረስ ነበረ፤ በፈረሱም ላይ፣ “ታማኝና እውነተኛ” የሚባል ተቀምጦ ነበር፤ እርሱም በጽድቅ ይፈርዳል፤ ይዋጋልም። ዐይኖቹ እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፤ በራሱም ላይ ብዙ ዘውዶች አሉ። ከርሱ በቀር ማንም የማያውቀው ስም በርሱ ላይ ተጽፏል። እርሱ በደም የተነከረ ልብስ ለብሷል፤ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ነው። የሰማይም ሰራዊት ነጭ፣ ንጹሕና ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ ለብሰው፣ በነጫጭ ፈረሶች ላይ ተቀምጠው ይከተሉት ነበር። ሕዝቦችን የሚመታበት ስለታም ሰይፍ ከአፉ ወጣ፤ “በብረት በትርም ይገዛቸዋል።” እርሱም ሁሉን ቻይ የሆነውን የእግዚአብሔርን የብርቱ ቍጣ ወይን መጭመቂያ ይረግጣል። በልብሱና በጭኑ ላይ እንዲህ የሚል ስም ተጽፏል፤ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶችም ጌታ። ቀጥሎም አንድ መልአክ በፀሓይ ውስጥ ቆሞ አየሁ፤ እርሱም በሰማይ መካከል ለሚበርሩ ወፎች ሁሉ እንዲህ ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ “ኑ፤ ወደ ታላቁ የእግዚአብሔር እራት ተሰብሰቡ፤ የምትሰበሰቡትም የነገሥታትን ሥጋ፣ የጦር አዛዦችን ሥጋ፣ የብርቱ ሰዎችን ሥጋ፣ የፈረሶችንና የፈረሰኞችን ሥጋ እንዲሁም የሰዎችን ሁሉ፣ ይኸውም የጌቶችንና የባሮችን፣ የታናናሾችንና የታላላቆችን ሥጋ እንድትበሉ ነው።” ከዚህ በኋላ አውሬው፣ የምድር ነገሥታትና ሰራዊታቸው በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሰራዊቱ ጋራ ለመዋጋት ተሰብስበው አየሁ። ነገር ግን አውሬው ተያዘ፤ ከርሱም ጋራ በፊቱ ምልክቶችን ያደርግ የነበረው ሐሰተኛው ነቢይ ተያዘ። በእነዚህ ምልክቶች የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትንና ለምስሉ የሰገዱትን አሳተ። ሁለቱም በሕይወት እንዳሉ በዲን ወደሚቃጠለው የእሳት ባሕር ተጣሉ። የቀሩት ደግሞ በፈረሱ ላይ ከተቀመጠው አፍ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ፤ ወፎችም ሁሉ ከሥጋቸው በልተው ጠገቡ።
ራእይ 19 ያንብቡ
ያዳምጡ ራእይ 19
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ራእይ 19:6-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos