የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 19:11-20

ራእይ 19:11-20 NASV

ከዚያም ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆ አንድ ነጭ ፈረስ ነበረ፤ በፈረሱም ላይ፣ “ታማኝና እውነተኛ” የሚባል ተቀምጦ ነበር፤ እርሱም በጽድቅ ይፈርዳል፤ ይዋጋልም። ዐይኖቹ እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፤ በራሱም ላይ ብዙ ዘውዶች አሉ። ከርሱ በቀር ማንም የማያውቀው ስም በርሱ ላይ ተጽፏል። እርሱ በደም የተነከረ ልብስ ለብሷል፤ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ነው። የሰማይም ሰራዊት ነጭ፣ ንጹሕና ከተልባ እግር የተሠራ ቀጭን ልብስ ለብሰው፣ በነጫጭ ፈረሶች ላይ ተቀምጠው ይከተሉት ነበር። ሕዝቦችን የሚመታበት ስለታም ሰይፍ ከአፉ ወጣ፤ “በብረት በትርም ይገዛቸዋል።” እርሱም ሁሉን ቻይ የሆነውን የእግዚአብሔርን የብርቱ ቍጣ ወይን መጭመቂያ ይረግጣል። በልብሱና በጭኑ ላይ እንዲህ የሚል ስም ተጽፏል፤ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶችም ጌታ። ቀጥሎም አንድ መልአክ በፀሓይ ውስጥ ቆሞ አየሁ፤ እርሱም በሰማይ መካከል ለሚበርሩ ወፎች ሁሉ እንዲህ ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ “ኑ፤ ወደ ታላቁ የእግዚአብሔር እራት ተሰብሰቡ፤ የምትሰበሰቡትም የነገሥታትን ሥጋ፣ የጦር አዛዦችን ሥጋ፣ የብርቱ ሰዎችን ሥጋ፣ የፈረሶችንና የፈረሰኞችን ሥጋ እንዲሁም የሰዎችን ሁሉ፣ ይኸውም የጌቶችንና የባሮችን፣ የታናናሾችንና የታላላቆችን ሥጋ እንድትበሉ ነው።” ከዚህ በኋላ አውሬው፣ የምድር ነገሥታትና ሰራዊታቸው በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሰራዊቱ ጋራ ለመዋጋት ተሰብስበው አየሁ። ነገር ግን አውሬው ተያዘ፤ ከርሱም ጋራ በፊቱ ምልክቶችን ያደርግ የነበረው ሐሰተኛው ነቢይ ተያዘ። በእነዚህ ምልክቶች የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትንና ለምስሉ የሰገዱትን አሳተ። ሁለቱም በሕይወት እንዳሉ በዲን ወደሚቃጠለው የእሳት ባሕር ተጣሉ።