መዝሙር 9
9
መዝሙር 9#9 መዝ 9 እና 10 በመጀመሪያው የጥንት ቅጅ ላይ አንጓዎቹ ተከታታይ ፊደላት ባሉት የዕብራይስጥ ሆህያት የሚጀምሩ እንዲሁም ጅማሬው ወይም መጨረሻው ትርጕም ዐዘል የሆነ አንድ ወጥ ግጥም ነበር፤ በሰብዓ ሊቃናት ውስጥ ሁለቱም አንድ መዝሙር ናቸው።
በክፉ ላይ ፍርድ
ለመዘምራን አለቃ፤ በሙትላቤን ቅኝት፤ የዳዊት መዝሙር።
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፤
ስለ ድንቅ ሥራዎችህም ሁሉ እናገራለሁ።
2በአንተ ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አደርጋለሁ፤
ልዑል ሆይ፤ ስምህን በመዝሙር እወድሳለሁ።
3ጠላቶቼ ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜ፣
ተሰነካክለው ከፊትህ ይጠፋሉ፤
4ፍርዴም ጕዳዬም በአንተ እጅ ናቸውና፤
ቅን ፍርድ እየሰጠህ በዙፋንህ ላይ ተቀምጠሃል።
5ሕዝቦችን ገሠጽህ፤ ክፉዎችንም አጠፋህ፤
ስማቸውንም እስከ ወዲያኛው ደመሰስህ።
6ጠላቶች ለዘላለም ጠፉ፤
ከተሞቻቸውንም ገለባበጥሃቸው፤
መታሰቢያቸውም ተደምስሷል።
7 እግዚአብሔር ግን ለዘላለም በዙፋኑ ላይ ነው፤
መንበሩንም ለፍርድ አጽንቷል።
8ዓለምን በጽድቅ ይዳኛል፤
ሕዝቦችንም በፍትሕ ይገዛል።
9 እግዚአብሔር ለተጨቈኑት ዐምባ ነው፤
በመከራም ጊዜ መጠጊያ ይሆናቸዋል።
10ስምህን የሚያውቁ ይታመኑብሃል፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ የሚሹህን አትተዋቸውምና።
11በጽዮን ለሚኖር ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤
ሥራውንም በሕዝቦች መካከል በግልጽ አውሩ፤
12ደም ተበቃዩ ዐስቧቸዋልና፤
የጭቍኖችንም ጩኸት አልዘነጋም።
13 እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላቶቼ የሚያደርሱብኝን መከራ ተመልከት፤
አይተህም ራራልኝ፤ ከሞት ደጅም አንሥተህ መልሰኝ፤
14ይህን ስታደርግልኝ፣ በጽዮን ሴት ልጅ ደጅ፣
ምስጋናህን ዐውጃለሁ፤
በማዳንህም ሐሤት አደርጋለሁ።
15አሕዛብ በቈፈሩት ጕድጓድ ገቡ፤
እግራቸውም ራሳቸው በስውር ባስቀመጡት ወጥመድ ተያዘ።
16 እግዚአብሔር በትክክለኛ ፍርዱ የታወቀ ነው፤
ክፉዎችም በእጃቸው ሥራ ተጠመዱ። ሒጋዮን#9፥16 ወይም በተመሥጦ ማሰብ ሴላ
17ክፉዎች ተመልሰው ወደ ሲኦል#9፥17 ወይም መቃብር ይወርዳሉ፤
እግዚአብሔርን የሚዘነጉ ሕዝቦችም ሁሉ እንደዚሁ።
18ችግረኞች ግን መቼም ቢሆን አይረሱም፤
የድኾችም ተስፋ ለዘላለም መና ሆኖ አይቀርም።
19 እግዚአብሔር ሆይ ተነሥ፤ ሰውም አያይል፤
አሕዛብም በፊትህ ይፈረድባቸው።
20 እግዚአብሔር ሆይ፤ ድንጋጤ አምጣባቸው፤
ሕዝቦች ሰው ከመሆን እንደማያልፉ ይወቁ። ሴላ
Currently Selected:
መዝሙር 9: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.